ቢቢሲ ለ2024 ከመላው ዓለም 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ እና አርዓያ ሴቶችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
ከእነርሱም መካከል የሰላም ኖቤል ተሸላሚዋ ሎሬት ናድያ ሙራድ፣ ከፆታዊ ጥቃት ያገገመችው እና የመብት ተሟጋቿ ጊሴሌ ፔሊኮት፣ ተዋናይት ሻሮን ስቶን፣ የኦሊምፒክ አትሌቶቹ ሬቤካ አንድራዴ እና አሊሰን ፌሊክስ፣ ድምጻዊት ራዬ፣ ሠዓሊ ትሬሲ ኤሚን፣ የአየር ጠባይ መብት ተሟጋቿ አዴኒኬ ኦላዶሱ እና ደራሲ ክርስቲና ሪቬራ ጋርዛ ይገኙበታል።
በጋዛ፣ በሊባኖስ፣ በዩክሬን እና በሱዳን ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች እና ሰብዓዊ ቀውሶችን ከመጋፈጥ ጀምሮ፣ በዓለም ላይ ከተካሄዱ በርካታ ምርጫዎች ጋር በተያያዘ ዋልታ ረገጥ የማኅበረሰብ አመለካከቶችን የተመለከቱት ሴቶች አዲስ የጥንካሬ ደረጃን ለማግኘት በጥልቀት ሀሰሳ ማድረግ ያስፈልጋል።
የቢቢሲ 100 ሴቶች ይህ ዓመት በሴቶች ላይ ያስከተለው አሉታዊ ተጽዕኖ በዙሪያቸው ያለው ዓለም ሲለወጥ እነርሱም ለለውጥ ለሚተጉትን እውቅና ይሰጣል። ይህ ዝርዝር የአየር ንብረት ድንገተኛ አደጋን ተፅእኖ ለመፈተሽ፣ የአየር ንብረት መብት አቀንቃኞች የሚኖሩበት ማኅበረሰብ ተጽዕኖውን እንዲላመድ እና መቋቋም እንዲችል የሚሠሩትንም ለማሳየት ቁርጠኛ ነው።
ስሞቹ የተዘረዘሩት በቅደም ተከተል አይደለም።
የቅርስ ጥበቃ መሀንዲስ
በየመን ለዓመታት በዘለቀው ጦርነት የተነሳ በርካታ ታሪካዊ ሕንጻዎች ስለወደሙ ኢንጂነር ሀሪቢያ አል ሂማሪ አዲስ ሕይወት ልትዘራባቸው ስራ ጀምራለች።
ከዩኔስኮ እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር፣ በቀድሞዋ ሰነዓ እና በአጠቃላይ አገሪቱ በርካታ የመኖርያ እና የቅርስ ሕንጻዎችን ጠግናለች።ዩኔስኮ ከ16ሺህ በላይ ስፍራዎች መውደማቸውን ባደረገው ቅኝት አረጋግጧል።
የቅርስ ጥበቃ ሥራዋ ታሪካዊ ስፍራዎች እንዲጠበቁ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የበርካቶችን አኗኗርም የለወጠ ነው።
አል ሂማሪ የአካባቢው ነዋሪዎችን በባህላዊ ዕደ ጥበባት የምታሰለጥን ሲሆን ወጣት ሴቶችም ወደ ሙያው እንዲገቡ ታበረታታለች።
ገጣሚ
ፀሐፊ እና ጋዜጠኛ ማሪያ ቴሬሳ ሆርታ ከፖርቹጋል ታዋቂ የሴት መብት ታጋዮች አንዷ እና በርካታ ሽልማት ያሸነፉ መጽሐፍት ደራሲ ነች። ነገር ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ በይበልጥ ‘ኖቫስ ካርታስ ፖርቹጋልስ’ (አዲሶቹ የፖርቹጋል ደብዳቤዎች) መጽሐፍን በጋራ በመጻፍ ትታወቃለች።
በአውሮፓውያኑ በ1972 የፖርቹጋል አምባገነን መንግሥት የልቦለድ፣ የግጥም እና የወሲብ ቀስቃሽ ጽሑፎችን ሲያግድ፣ ሆርታ እና ሌሎች ደራሲዎች ከማኅበረሰብ ወግና ባህል ያፈነገጠ ጽሑፍ በመጻፍ "የፕሬስ ነፃነትን አላግባብ ተጠቅመዋል" በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
የሦስቱ ማሪያዎች ጉዳይ በሚል የበለጠ የሚታወቁት ደራሲዎች ታሪክ መነጋገርያ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲካሄድ ምክንያት ሆኗል።
ጉዳያቸው በፍርድ ቤት መታየት ያቆመው እኤአ በ1974 የካርኔሽን አብዮት ስርዓቱ እንዲወርድ ካደረገ በኋላ ነበር። ይህ ታሪካዊ ጉዳይ ከተከሰተ ዘንድሮ 50 ዓመት ሞልቶታል።
የሃይማኖት ተሟጋች
አናት ሆፍማን በአይሁድ እምነት ውስጥ ስለ ጾታ እኩልነት እና የሃይማኖቶች መቻቻል ለዓመታት ስትሟገት ቆይታለች።
በኢየሩሳሌም ጥንታዊ ከተማ አይሁድ ሴቶች እኩል የመፀለይ መብት እንዲኖራቸው የሚታገለው የ'ዉሜን ኦፍ ዘ ዎል ግሩፕ' መስራች አባል ናት። ላለፉት ረዥም ዓመታት ቶራህን ማንበብ እና ሴቶች ለፀሎት የሚለበሰውን ሻርፕ እንዳይለብሱ የሚከለክሉ መመርያዎችን ስትታገል ቆይታለች።
ሆፍማን ላለፉት 20 ዓመታት እኩልነትን እና ማኅበራዊ ፍትህን ለማስፈን የሚካሄደው እንቅስቃሴ፣ የሕግ እና የግንዛቤ ክንፍ በመሆን የሚያገለግለውን የ'እስራኤል ሪሊጂየስ አክሽን ሴንተር' ዳይሬክተር ሆና አገልግላለች።
ከዚያ ቀደም ብሎ በኢየሩሳሌም ከተማ ምክር ቤት ውስጥ በነበራት መቀመጫ የኖሩ ፖሊሲዎችን ትሞግት ነበር።
የሥነ ሕንጻ ባለሙያ
ሌዝሊ ሎኮ “ሥነ ሕንፃን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ” የሚለው ሥራዋ በሙያዋ ትልቅ ክብር የሆነውን፣ ከብሪቲሽ አርክቴክቶች ሮያል ኢንስቲትዩት የ2024 የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቶላታል። ይህም ብቻ ሳይሆን ኢንስቲትዩቱ በ1848 ከተመሠረተ ወዲህ ሽልማቱን የተቀበለች የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴትም ሆናለች።
ላለፉት ሁለት አስርታት እምብዛም ውክልና ካልተሰጣቸው ማኅበረሰቦች የሚመጡ ሰዎች ወደፊት አንዲመጡ በማድረግ ትሰራለች።
የጋና-ስኮትላንዳዊዋ አካዳሚም የ’ቬኒስ ቢየናሌ ኦፍ አርክቴክቸር’ን በማዘጋጀት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሴት ሆናለች። በዚህ ዝግጅት ላይም ከካርቦን የጸዳ እና ከቅኝ ግዛት የመላቀቅ ጭብጦች ላይ ትኩረት አድርጋለች።
በአክራ መቀመጫውን ያደረገው አፍሪካን ፊውቸርስ ኢንስቲትዩት መስራች ስትሆን፣ ሥነ ሕንጻ፣ ማንነት እና የዘር ግንኙነት ላይ ትኩረት ያደርጋል።
ጥንካሬ ማለት ምንም እንኳ ውጣ ውረዱ አድካሚ ቢሆንም፣ ግዴለሽነት ቢኖር፣ ከተቃውሞ የበለጠ ለመቋቋም ፈታኝ ቢሆንም፣ ከመስመር ሳይለቅቁ መቆየት ነው።
ሌዝሊ ሎኮ
የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች
ስለ ጾታ ምርጫዋ፣ በግልጽ ለሁለቱም ጾታ ፍቅር እንዳላት (ፓንሴክሹዋል) የምትናገረው እና ተደራራቢ የጡንቻ መደደር ሕመም የሚያጠቃት ሮክሲ ሙሬይ፣ ባላት መድረክ ሁሉ ስር የሰደደ ሕመም ያለባቸውን ሰዎች ለማበረታታት እና በሕክምና፣ በበጎ አድራጎት እና በተቋማት የሚደርስባቸውን መገለል በመቃወም ትናገራለች።
የሙሬይ አክቲቪዝም የሚጠቀመው ለፋሽን ያላትን ዳራ ሲሆን፣ ዘናጭ የሆኑ የአካል ድጋፎችን እንዲያገኙ፣ የአካል ጉዳት ያለባቸው እና አነስተኛ ቁጥር እና ከተለያየ ብሔር ለሚመጡ ቡድኖች ተሰሚነት እንዲያገኙ ትሰራለች።
ዘ ሲክ ኤንድ ሲክኒንግ' የተሰኘው ፖድካስት መስራች ስትሆን ከአካል ጉዳት ጋር የሚኖሩ ሰዎች ታሪክ፣ ሕመም ምንም ሳይሸፋፈን እንደወረደ የሚቀርብበት ዝግጅት ነው።
ነጭ ሳልሆን፣ የተመሰሳይ ጾታ አፍቃሪ እና የአካል ጉዳተኛ ሆኜ ጥንካሬ ማለት በጣም የግል እና በመሰረታዊነት ደግሞ የጋራ ነው። እንደ እኔ የተገለሉ ሰዎች ስርዓቶችን የመገዳደር ብርታታቸው ነው።
ሮክሲ ሙሬይ
ተጓዥ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ
በ56 ዓመቷ ጥቃት ከነበረበት የትዳር ሕይወት ነጻ የወጣችው ሱ ሚን፣ የጡረታ ገንዘቧን፣ መኪናዋን እና ማረፍያ ድንኳኗን ይዛ በቻይና ብቻዋን መጓዝ ጀመረች።
ጉዞዋን ከጀመረችበት 2020 ጀምሮ ከ20 በላይ አውራጃዎች የሚገኙ 100 ከተሞችን አይታለች።
ጉዞዋን በአግባቡ የምትሰንድ ሲሆን፣እንደሷ ያሉ በእድሜ የገፉ ሴቶችን፣ ከተለመደው ወጣ ባለ መልኩ ማነሳሳቱን ተከትሎ ታሪኳ በማኅበራዊ ሚድያ ላይ ሞቅ ያለ ክርክር አስነስቷል።
በሶሻል ሚዲያ አካውንቶቿ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሏት ሲሆን፣ የሕይወት ታሪኳ 'ላይክ ኤ ሮሊንግ ስቶን' የሚል ርዕስ ተሰጥቶት ወደ ፊልም ተቀይሯል። በዚህ ዓመት ለእይታ ይበቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የሜካፕ ባለሙያ
ኦሊቪያ ማክቬይ አሎፔሺያ (alopecia) እንዳለባት ካወቀች በኋላ ሰው ሰራሽ ጸጉሮችን (ዊግ) መሞከር ጀመረች። በድረገጽ ላይ አዳዲስ አሰራሮችን እና አማራጭ ፀጉሮችን በመሞከር፣ የፀጉር መርገፍ የሚገጥማቸውን ሴቶች ታበረታታለች።
ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮች ያሏት ሲሆን፣ ስለ አሎፒሺያ እና ሴቶች ጤና ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባሻገር ዊግ መጠቀም ነውር እንዳልሆነ ታስተምራለች።
ማክቬይ በሰሜን አየርላንድ የሜካፕ ባለሙያ እና የማኅበራዊ ሚድያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ስትሆን ፀጉሯ መርገፍ የጀመረው ገና አፍላ ጎረምሳ እያለች ነው።
አሁን ስለ ዊግ የሚዘጋጁ ወርክሾፖችን ታዘጋጃለች፣ እንዲሁም ዳግም በራስ መተማመንን ስለማግኘት የራሷን ተሞክሮ ታስረዳለች፤ አሎፔሺያ ታማሚ የሆኑ ሴቶች በጋራ በመሆን በሕመማቸው ዙርያ እንዲወያዩ እና እንዲበረታቱ ታደርጋለች።
ጥንካሬ እኛ ሴቶች እንደ ዘውድ የምንደፋው ነገር ነው። በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን፣ ለምንጊዜም ከራሳችን ጋር የምናዋህደው፣ የምንለውጠው እና በዙሪያችን ካለ ነገር አንጻር የምንማረው ነው።
ኦሊቪያ ማክቪህ
ዲዛይነር
የፋሽን ዲዛይነሯ ያዝሚን ምጃሊ ሥራዎቿ ከፍልስጤም ባሕል እና ሕይወት የተቀዱ ናቸው።
በአሜሪካ ደቡባዊ ክፍል ያደገች ቢሆንም፣በ2020 ድርጅቷን በከፈተችበት ዌስት ባንክ፣ ራማላ መኖር ጀምራለች።
የፋሽን ድርጅቷ በቤተሰብ ከሚተዳደር የልብስ ስፌት ወርክሾፕ ጋር ነው የሚሰራው። የአገሬው የቅመማ ቅመም ሱቆች ጨርቆችን ለማቅለም የሚያግዙ ቅመሞችን፣ የሴቶች ማኅበራት ደግሞ በጋራ በመሆን የሚያስፈልጉ ጨርቆችን ያቀርባሉ። ሸማኔዎች፣ የስፌት ባለሙያዎች፣ የጥልፍ ባለሙያዎች፣ እና ቆራጮች ባሕላዊ ቴክኒኮችን በመጠቀም የፍልስጤም ዕደ ጥበብ የበለጠ ዕይታ ይሰጡታል።
ምጃሊ ልብሶቿን የፍልስጤማውያንን ታሪኮች ለመናገር ትጠቀምባቸዋለች። በዓለም ላይ ሴቶች በመንገዶች ላይ የሚገጥማቸውን ጾታዊ ትንኮሳ ለማሳየት፣ በጃኬቶች እና ቲ ሸርቶች ላይ 'ኖት ዩር ሀቢብቲ' (ያንተ ልጅ አይደለሁም) የሚል ጽፋ መልዕክት ታስተላልፋለች።
ከሞኒውመንታል ዌልሽ ውሜን መስራቾች መካከል አንዷ
ከ2021 በፊት፣ በዌልስ ለአገሬው ሴቶች የቆመ አንድም ሀውልት አልነበረም።
ከዚህ በመነሳት ጠበቃዋ ሄለን ሞሊኔክስ ለትርፍ ያልተቋቋመውን ሞኒውመንታል ዌልሽ ውሜንን ከሌሎች ጋር የመሰረተች ሲሆን፣ የዌልሽ ሴቶች አበርክቶን፣ ስኬትን እና በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ውክልና ለማሻሻል ትሰራለች።
ከሕዝብ በተሰጠ አስተየየት ላይ በመነሳት፣ ሞሊኔክስ እና ቡድኖቿ፣ አምስት የሴት ሀውልቶችን በማቆም ታሪካቸው ተረስቶ እንዳይቀር ለማድረግ አቅደዋል።
ቡድኑ እስካሁን ድረስ አራት ሀውልት አቁሟል።
ጋዜጠኛ
ሂንዳ አብዲ ከታዳጊነቷ ጀምሮ ጎበዝ ፀሐፊ የነበረች ሲሆን፣ ከጂግጂጋ ወደ ሐርጌሳ ግጭትን ሸሽተው ቀያቸውን ጥለው ስለሚሄዱ ሰዎች የሚገልጹ ታሪኮችን በማስታወሻ ደብተሯ ላይ ትሰንድ ነበር።
አሁን ለአገሪቱ የመጀመርያ የሆነ እና 'ቢላን' የተሰኘ በሴቶች ብቻ የሚዘጋጅ መገናኛ ብዙኃን ዋና አዘጋጅ ነች።
ቡድኑ የተደራጀው የሶማሊያ ሴቶች በሥራ ቦታ የሚያጋጥሟቸውን ከፍተኛ ፆተኝነት እና ትንኮሳ፣ በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው ሪፖርት ላይ እነዚህ ተግዳሮቶች መኖራቸው ተጠቅሷል፣ ለመዋጋት በማሰብ ነው።
ቢላን ለጋዜጠኞች አደገኛ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ሶማሊያ በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራ ነው። ዘገባዎቹ ኤችአይቪ በደማቸው ያለ እና ተደብቀው የሚኖሩ ሰዎችን ታሪክ፣ ጥቃት የሚደርስባቸው ወላጅ አልባ ሕጻናትን፣ እንዲሁም በማኅበረሰቡ የተገለሉ አልቢኖዎች ላይ ያተኩራሉ።
የፎቶግራፍ ባለሙያ
በደረቁ ወንዞች እና የተበላሹ ሰብሎች ገጽታ ላይ በመስራት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያዊቷ ፎቶግራፍ አንሺ ማህደር ኃይለስላሴ፣ በኢትዮጵያ ያሉ ቤተሰቦች ድርቅ ምን ያህል ሴት ልጆቻቸውን ለጋብቻ እንዲሰጡ እንዳደረጋቸው ሰንዳለች። በዚህም ሥራዋ በ2023 ‘ኮንቴምፖረሪ አፍሪካን ፎቶግራፉ ፕራይዝ’ አሸናፊ ሆናለች።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ በ2050 በአየር ንብረት ቀውሱ ምክንያት ላለ እድሜ ጋብቻ የተጋለጡ ልጃገረዶች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሲሶ ይጨምራል ብለው ይገምታሉ።
የኃይለ ሥላሴ ፎቶግራፍ ሥራ በየዕለቱ አብራ ከምታሳልፋቸው ሰዎች ታሪክ እና ልምድ ላይ መሰረት ያደረገ ነው።
ሥራዎቿ በትልልቅ መድረኮች፣ በአፍሪካ ቤይናሌ ፎቶግራፊ ጨምሮ፣ ለእይታ በቅቷል።
የፋሽን ስራ ፈጣሪ
የግራፊክ ዲዛይን ባለሙያዋ አይዲያና ዴል ሪዮ ከሌሎች ጋር ሆና የመሰረተችው ክላንዴስታይን፣ ልብሶችን ወደ ዓለም ገበያ አቅርቦ በመሸጥ የመጀመርያው የኩባ ድርጅት ነው።
ኩባንያው የተጀመረው ፕሬዝዳንት ራውል ካስትሮ ነጻ ቢዝነስ እና ንግድ ላይ የነበረውን ደንብ ካላሉ በኋላ ነው።
መቀመጫቸውን በሀቫና ባደረጉ እና በርካቶቹ ሴቶች በሆኑ ዲዛይነሮች የተሰሩት ምርቶች፣ የኩባን ባህል የሚያሳዩ፣ የደሴቲቱን ፈጠራ ለማበረታታት እና ለማድነቅ ዓላማ አድርገው የተነሱ ናቸው። ዴል ሪዮ በኩባንያው የምርት ዑደት ውስጥ ዳግም ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሶችን የምትጠቀም ሲሆን ትኩረቷም ቀጣይነት ያለው ተግባር እንዲሆን ነው።
የሐቫና ኢንስቲትዩት ኦፍ ዲዛይን ምሩቅ ስትሆን፣ ወደ ፋሽን ቢዝነስ ከመግባቷ በፊት ለጋለሪዎች፣ ለቴአትሮች እና ፌስቲቫሎች ፖስተሮችን ዲዛይን ታደርግ ነበር።
የቀብር ሥነስርዓቶች ፈጻሚ
ፑጃ ሻርማ ላለፉት ሦስት ዓመታት በደልሂ ውስጥ ዘመድ አዝማዶቻቸው ያልተገኙላቸው አስከሬኖችን የግብዓተ መሬት ስርዓት ስትፈፅም ቆይታለች።
ይህንን ለመከወን ያነሳሳት የግል ልምዷ ነው። በአንድ ወቅት ወንድሟ ከተገደለ በኋላ የመጨረሻውን ከቀብር በፊት የሚፈጸም ሥርዓት ለማከናወን ማንም ሰው ሊረዳት ባለመምጣቱ ሥነ ሥርዓቱን ብቻዋን ለመፈጸም ተገድዳለች።
ይህ ተግባር በሂንዱ ሃይማኖት ልምድ መሰረት በወንዶች የሚከወን በመሆኑ፣ ሻርማ ከካህናቱ እና ከራሷ ማኅበረሰብ አባላት ተቃውሞ ገጥሟታል።
ተቃውሞ ቢገጥማትም ከ4,000 በላይ ለሚሆኑ የተለያዩ እምነትና ሃይማኖት ተከታዮች የቀብር ሥነሥርዓት ፈጽማለች። ሥራዎቿን በማኅበራዊ ድረ ገጽ በማጋራትም ለሁሉም ሰው ሞት ተገቢውን ክብር ለመስጠት ትታገላለች።
መነኩሴ
ሲስተር ኡጌንያ ቦኔቲ 100 መጠለያዎችን የረዱ ሲሆን፣ የሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑትን ሴቶች ለመርዳት የአፍሪካ መነኮሳት ጥምረትን መስርተዋል።
በሮም በወሲብ ንግድ እንዲሰማሩ የተገደዱ ሴቶችን በመርዳት በርካታ ለሊቶችን ያለ እንቅልፍ የሚያሳልፉት ኡጌንያ፣ 'ስሌቭስ ኖ ሞር' የተሰኘ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚሰራው ድርጅት ፕሬዝዳንት ናቸው።
ቦኔቲ በኬንያ ለ24 ኣመታት ሚሽነሪ ሆነው የሰሩ ሲሆን፣ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የባቡር ባለሥልጣናት የጸረ ሕገወጥ ሰዎች ዝውውር እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ አግዘዋል።
ጡረታ ከመውጣታቸው በፊት፣ በፖፕ ፍራንሲስ ትዕዛዝ የ2019ን ካቶሊኮች ዓመታዊ የስቅለት ሲያከብሩ በጋራ የሚያደርጉትን ጸሎት ጽፈዋል።
የሙዚየም ሥራ አስኪያጅ
የኪርጊስታንን ባሕላዊ ቅርሶች መጠበቅ እና ማደስ ለዛኒልሲንዛት ቱርጋንቤቫ ቅድሚያ የሚሰጥ ጉዳይ ነው።
በቢሽኬክ ልዩ የሆኑ ባሕላዊ ቅርሶችን የያዘ ሙዚየም የምትመራ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው ጎብኚዎችንም ይስባል።
የበጎ አድራጎት ሥራዋ አካል የሆነው ደግሞ የኪርጊዝ ሥነ ጽሑፍን መጠበቅ ነው። ይህም የ'ማናስ ኤፒክ' የሚሰኝ ሲሆን 40 ጎሳዎችን በኪርጊዝ ክልል ውስጥ አንድ ስላደረገ ጦረኛ የሚተርክ ነው።
በዩኔስኮ ከተመዘገቡት ግጥሞች መካከል አንዱ 500 ሺህ መስመሮች ያሉት ሲሆን፣ ከሆሜር ኦዲሴይ 20 እጥፍ የረዘመ፣በዓለማችን ላይ ካሉ ረዥም ኤፒኮች አንዱ ነው ተብሎ ይታመናል። የ ቱርጋንቤቫ ሥራ ይህንን የግጥም ስራ እየጠቀሱ ለሚያዝናኑ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የሥራ እድል ፈጥሯል።
ጋዜጠኛ እና ገጣሚ
የ22 ዓመቷ ፕሌስቲያ አላቃድ በጋዛ ጦርነት ሲጀመር ነው የዩኒቨርስቲ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው።በጦርነቱ የመጀመርያ ወቅቶች፣ በእስራኤል አየር ኃይል ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት ሲፈጸም መኝታ ቤቷ ሆና ራሷን ቪድዮ ቀርጻ ለቀቀች።
ከዚያም በርካታ ሰዎች ተቀባብለውት፣ በኢንስታግራም ገጿ ብቻ 4 ሚሊዮን ተከታዮችን አፈራች።በመቀጠልም ስለ ጋዛ ወቅታዊ መረጃዎችን፣ ግጥሞችን እና ማስታወሻዎችን ማጋራት ቀጠለች።በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋራቻቸውን ማስታወሻዎች መሰረት አድርጋ የጻፈችው "አይስ ኦፍ ጋዛ" በቅርቡ ለሕትመት ይበቃል።
አላቃድ በ2024 የዓለማችን ወጣት ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ናት። ስለ ፍልስጤማውያንም ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት የዓለም መንግሥታት ሰሚት ላይ ቀርባ ተናግራለች።
አላቃድ በሕዳር 2023 ጋዛን ለቅቃ ወጥታለች። በቤይሩት በሚድያ ስተዲስ የማስተርስ ዲግሪዋን እንድትማር ነጻ የትምህርት እድል አግኝታለች።
የትምህርት በሚድያ ሥራ ፈጣሪ
የአፍጋኒስታን ሴቶች በታሊባን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ሲከለከሉ፣ የሚድያ ሥራ ፈጣሪዋ ሐሚዳ አማን፣ መማር ላልቻሉ ተማሪዎች በኢንተርኔት ትምህርት የሚሰጠውን ቤጉም አካዳሚን ለመጀመር ወሰነች።
ባለፈው ዓመት ይህ የትምህርት መስጫ መድረክ ከ7ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ድረስ የሚሰጡ ትምህርቶችን የሚያስተምሩ፣ ከ8500 በላይ ቪዲዮዎችን በዳሪ እና ፓሻቶ ቋንቋዎች ሰርቷል።
አማን በመጋቢት ወር፣ ቤገም አካዳሚ በቻናሉ የሚያስተምራቸውን ትምህርቶች በሳተላይት ለማሰራጨት፣ ቤገም ቲቪን ጀምራለች።
ይህ አገልግሎት ታሊባን በ2021 ወደ ስልጣን ከተመለሰ ወዲህ የተጀመረውን እና በሴቶች ተዘጋጅቶ ለሴቶች የሚቀርበውን ቤገም ራዲዮ ፕሮጀክትን ተከትሎ የተጀመረ ነው።
የፎቶ ጋዜጠኛ
የፎቶ ጋዜጠኛዋ ክርስቲና አሲ በ1990ዎቹ፣ የእርስ በእርስ ጦርነት ካበቃ በኋላ በነበረ አለመረጋጋት ወቅት ነው በሊባኖስ ያደገችው። ይህም ነው ግጭቶችን እና በጦርነት ወቅት ያልተነገሩ ታሪኮችን እንድትሰንድ ያደረጋት።
በ2023 ጥቅምት ወር እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ድብደባ የተነሳ ሕይወቷ አሳዛኝ ሁኔታ ገጠመው።
ፍንዳታው ጋዜጠኛ ኢሳም አብደላህን ሲገደል፣ ሌሎች አምስት ባልደረቦቿ ተጎድተው፣ አሲ እግሯ ተቆርጧል።
ይህ ገጠመኟ ለጋዜጠኞች ደህንንት እንድትሟገት አድርጓታል። ለዚያም ነው በ2024 በፓሪስ የኦሎምፒክ ችቦ መለኮስ ላይ ስትሳተፍ መታሰብያነቱን በሥራ ላይ እያሉ ለሞቱ ጋዜጠኞች ያደረገችው።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች
ስቬትላና አኖኪና አብዛኛዎቹ ሙስሊም የሆኑ እንዲሁም ምሥራቅ አውሮፓን እና እስያን በሚያገናኘው አካባቢ የሚኖሩ የሩሲያ ሰሜን ካውካሰስ ማኅበረሰብ አባላት የተገኙ ከቤት ውስጥ ጥቃት ያመለጡ ተጎጂዎችን በመርዳት ዓመታትን አሳልፋለች።
በ2020 ከሌሎች በጎ ፈቃደኞች ጋር በመሆን ማሬም ፕሮጄክትን መሥርታለች። ይህ ፕሮጀክት ከዳግስታን፣ ከቼቺኒያ እና ከሌሎች የሰሜን ካውካሰስ ሪፐብሊኮች የሚመጡ ለአደጋ የተጋለጡ ሴቶችን ካሉበት ሁኔታ እንዲወጡ ያመቻቻል፤ ጊዜያዊ መጠለያ እንዲያገኙ ይረዳል። እንዲሁም የሕግ እና የሥነ-ልቦና ድጋፍ ይሰጣል ።
አኖኪና የቼቺኒያ እና የዳግስታን ፀጥታ ኃይሎች የሴቶች መጠለያዋን ከበረበሩ በኋላ በአውሮፓውያኑ 2021 ሩሲያን ለቅቃ ወጥታለች።
በባለፈው ዓመት የሩሲያን መከላከያ ኃይል ስምን በማጥፋት የወንጀል ምርመራ መዝገብ ከፍተውባታል።
አርቲስት
ትሬሲ ኢሚን እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ ውስጥ ‘ማይ ቤድ’ እና ‘ዘ ቴንት’ በሚሉ ሰዎች ፆታዊ ልምምዳቸውን እንዲያንጸባርቁ በሚጋብዙ ቀስቃሽ ሥራዎቿ ዝናን አግኝታለች።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በኪነ-ጥበብ ዓለም ውስጥ ስሟ ናኘ። በግለ ታሪክ እና ሁሉን እንደወረደ ገላልጠው በሚያሳዩ አቀራረቦቿም ተቀባይነትን አገኘች።
በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘንድ መከራከሪያ የሆነው ‘ማይ ቤድ’ የተሰኘው ሥራዋ ለመጀመሪያ ጊዜ በለንደን ከታየ 25 ዓመታት ሆኖታል። በብሪቲሽ የሥነ ጥበብ ማኅበረሰብ ዘንድ ወጣ ያለች ተብላ የተፈረጀችው ኢሚን፣ በዚህ ዓመት ለዕይታ ጥበባት ላደረገችው አስተዋጽኦ ከንጉሥ ቻርልስ የክብር ሽልማት ተበርክቶላታል።
አርቲስቷ አዳዲስ ባለተሰጥኦዎችን ለመንከባከብ በዩኬ ማርጌት ውስጥ ትሬሲ ኢሚን ፋውንዴሽንን አቋቁማለች።
በአሁኑ ጊዜ ሴት በመሆናችን፣ በተቻለን መጠን ጽናት የሚያስፈልገን ይመስለኛል… አሁን ለሴቶች የበለጠ አንድነት እና ትልቅ ትግል የምናደርግበት ጊዜ ይመስለኛል።
ትሬሲ ኢሚን
የአይሁድ የሃይማኖት መምህርት
በኒውዮርክ የአይሁድ ማኅበረሰብ ዘንድ ፈር ቀዳጅ የሆነችው የሃይማኖት መምህርቷ ሻሮን ኪሌንባም፣ ለሦስት አስርታት የተመሳሳይ ጾታ አፍቃርያን እና ሃይማኖት ላይ ያለው አተያይ እንዲለወጥ ታግላለች።
በ1992 የመጀመርያዋ የሃይማኖት መምህርት ሆና የተሾመችው ኪሌንባም፣ ማኅበረሰቡን በ1990ዎቹ የነበረውን የኤድስ ቀውስ ጨምሮ፣በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ መርታዋለች።
የምታገለግለው ማኅበረ ምዕመናን የተመሳሳይ ጾታ አፍቃርያንን በአባልነት እንዲቀበል ያደረገች ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ የጾታ ምርጫቸው የተለያየ ለሆኑ በርካታ ሰዎች ምቹ የሆነ ምኩራብ ተብሎ ይጠቀሳል።
በዚህ ዓመት በጡረታ የተገለለችው ኪሌንባም፣ከበርካታ ማኅበራዊ ለውጥ ፕሮጀክቶች ጀርባ ያለች ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የሃይማኖቶች ነጻነት ኮሚሽን ውስጥ ሾመዋታል።
ደስታ የመንፈሳዊ እና የፖለቲካ ተቃውሞ ሥራ ነው።
ሻሮን ኪሌንባም
ልብስ ሰፊ እና ነጋዴ
ከሁለት ዓመት በፊት፣ ዲሎሮም ዩልዶሼቫ ሁለት እግሮቿን ሰብል ስብሰባ ላይ ሳለች አጣች።ነገር ግን ይህ አደጋ ትልቅ ከማለም አላቆማትም።
ወጣት የኡዝቤክ ሴቶች ገቢ የሚያገኙበት አዲስ ክህሎት መማር ፈለገች፤ ስለዚህ የራሷን የልብስ ስፌት ንግድ ለማቋቋም ወሰነች።
መሠረታዊ የሆነውን የሥራ ፈጠራ እና የሀብት አስተዳደር ተምራ 40 ስራ ፈላጊዎችን አሰለጠነች።በወራት ውስጥ ድርጅቷ በፍጥነት የተመነደገ ሲሆን፣ ነጻ ወንርክሾፖችን ማካሄድ ብቻ ሳይሆን፣ ለተማሪዎች እና ለሠራተኞች የደንብ ልብሶችን እንዲያመርት የሥራ ስምምነቶችን አድርጓል።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሥራዋ ለእርሷ እና ለበርካታ ሴቶች የገቢ ምንጭ ሆኗል።
የፊልም ባለሙያ
ሺን ዳኤዋ ሽልማቶችን ያገኘ ዘጋቢ ፊልም የሰራች ባለሙያ ስትሆን በቦርሳዋ ድሮን በመገኘቱ በቁጥጥር ስር ውላለች።
ወታደራዊ አገዛዝ በሰፈነባት ምያንማር በዚህ ዓመት ፍርድ ቤት ቀርባ የአገሪቱን ጸረ ሽብር ሕግ በመተላለፍ ተወንጅላለች። ጉዳይዋ ያለምንም ጠበቃ በዝግ ችሎት የታየ ሲሆን፣ እድሜ ልክም ተፈርዶባታል።
የፊልም ባለሙያዋ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1988 ጀምሮ ወታደራዊ አገዛዝን የምትቃወም ሲሆን ለእስርም አዲስ አይደለችም።
በርካታ አጫጭር ዘጋቢ ፊልሞችን ያዘጋጀች ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ የዓለም አቀፍ ተመልካቾችን ዓይን መሳብ ችለዋል። ከእነዚህም መካከል በ2007 የሰራችው እና የቡድሀ መነኮሳትን ጨምሮ ወታደራዊ አገዛዝን ተቃውመው፣ ዲሞክራሲን ለመጠየቅ አደባባይ ስለወጡ ሰልፈኞች የሚያትተው ፊልሟ ይጠቀሳል።
ማሕበራዊ አክቲቪስት
የተዋናይት ጆሀና ባሀሞንን ሕይወት የተቀየረው የኮሎምብያን ማረሚያ ቤት ከጎበኘች በኋላ ነው። ከዚያም በኋላ 'ሁለተኛ እድል' በሚፈልጉ ሰዎች ላይ ለመሥራት ተነሳሳች።
በ2012 የትወና ሙያዋን ትታ የማረሚያ ቤቶች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ መወትወት የጀመረች ሲሆን፣ በኮሎምቢያ ማረሚያ ቤቶች ያሉትን እና ከእስር የተፈቱትን የሚደግፍ ፋውንዴሽን አቋቋመች።
ፋውንዴሽኑ በመላ አገሪቱ በ132 ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ከ150 ሺህ በላይ ሰዎችን አገልግሏል።
የማሕበራዊ አክቲቪስቷ በ2022 የቀረበውን እና የጆሀና ባሀሞን ሕግ በመባል የሚታወቀውን፣ የኢኮኖሚ ድጎማ፣ የቅጥር እድል፣ እና የእስር ዘመናቸውን ለጨረሱ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ የሚያደርገውን 'የሁለተኛ እድል ሕግ' ደግፋ ዘመቻዎችን አድርጋለች።
ጠንካራ መሆን ከችግር በኋላ ከመነሳት እና ወደ ፊት ከመሄድ ያለፈ ነው፤ ራስን ለመቀየር ውሳኔ መወሰንን ያካትታል።
ጆሀና ባሀሞን
የሴቶች መጠለያ ሥራ አስኪያጅ
በአይስላንድ የሴቶች መጠለያ ውስጥ፣ ሊንዳ ድሮፍን ጉናርስዶቲር፣ በቤት ውስጥ ጥቃት ምክንያት ቤታቸውን ለቅቀው ለመውጣት የተገደዱትን ትደግፋለች።
አይስላንድ ብዙውን ጊዜ "ለሴቶች ምቹ ቦታ" ተብላ የተመረጠች አገር ነች። ይኹን እንጂ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በተከታታይ ከፍ ብለው የቀጠሉባት አገር ናት።
የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆኗ ፕሮጀክቱ አዲስ የአይስላንድ የመጀመሪያ ታቅዶ የተገነባ የሴቶች መጠለያን ትመራለች ።
ድሮፍን ጉናርስዶቲር እንዳለችው ከ20 ዓመት በፊት በመጠለያው ከቆዩት ሴቶች 64% የሚሆኑት በመጨረሻ ወደ አጥቂዎቻቸው ይመለሱ ነበር፤ ነገር ግን ይህ አሃዝ አሁን በተሻሻለ ድጋፍ እና አገልግሎት ወደ 11% ዝቅ ብሏል።
ደራሲ
ታዋቂዋ ደራሲ ክሪስቲና ሪቬራ ጋርዛ ለበርካታ ዓመታት፣ የ2024 የፑሊትዘርን ጨምሮ ብዙ ሽልማቶችን አግኝታለች። የፑልቲዘሩን ሽልማት ያገኘችው ‘ሊሊያናስ ኢንቪዝብል ሰመር’ በተሰኘው መጽሐፏ የሴቶችን ግድያ ጭብጥ አድርጋ በመጻፏ ነው።
እኤአ በ1990ዎቹ ሜክሲኮ በቀድሞ የወንድ ጓደኛ በተገደለችው እህቷ ሊሊያና ታሪክ ላይ ያተኮረው መጽሐፍ፣ ገዳይ ፍቅረኛዋ ሸሽቶ ለፍርድ ሳይቀርብ መቅረቱን ያስነብባል። ደራሲዋ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለውን አሰቃቂ ሁኔታ ተጋፍጣ፣ በዓለም ላይ ሴቶች በከፍተኛ ቁጥር በሚገደሉባት አገር ፍትህ ለማግኘት ስትጥር ያሳያል።
ሪቬራ ጋርዛ በሂዩስተን ዩኒቨርሲቲ በስፓኒሽ ቋንቋ የፈጠራ ጽሑፍ የፒኤችዲ ፕሮግራም መሥራች እና ሊቀመንበር ነች።
ቋንቋን በተከታታይ እና በጥልቀት ለመጠቀም መሞከር፣ በመጨረሻም የሴቶችን ታሪክ በምልዓት እንዲያስተላልፍ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ዓይነት ፅናት መሠረት ይጥላል።
ክርስቲና ሪቬራ ጋርዛ
የሱፕ ኪችን መስራች
ማርጋሪታ ባሬንቶስ፣ 15 ሰዎችን ለመመገብ የጀመረችው ሱፕ ኪችን አሁን ከ5,000 በላይ ሰዎችን ይመግባል። ባሬንቶስ ከ46 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል 46 በመቶው ከድህነት ወለል በታች በሚኖርባት አርጀንቲና ረሀብን ለመዋጋት ተግታ ትሰራለች።
በድህነት በሚማቅቅ ክልል የተወለደችው ባሬንቶስ፣ ከልጅነቷ ጀምሮ የተለያዩ ችግሮችን ተጋፍጣለች። ሱፕ ኪችንን በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1996 የመሰረተች ሲሆን፣ አሁን የሕጻናት ማቆያ፣ የጤና ማዕከል፣ የልብስ ስፌት ወርክሾፕ እና ቤተ መጻሕፍት ያሉት ፋውንዴሽን ሆኗል።
ለማኅበረሰቡ የምትሰጠው ግልጋሎት ከተለያዩ ነጋዴዎች እና ታዋቂ ሰዎች ድጋፍ አስገኝቶላታል። በቅርቡም ሊዮኔል ሜሲ ፊርማው ያረፈበት ቲሸርቱን በጨረታ ሸጣ እንድትጠቀምበት ሰጥቷታል።
የፊልም ዳይሬክተር፣ ደራሲ እና የጋለሪ ባለቤት
ወደ 95ኛ ዓመቷ እየተቃረበች የምትገኘው ደራሲዋ እና ዳይሬክተሯ ዡዋን ፉዎንግ ጥንቅቅ ያለ ሕይወትን ኖራለች።
በቬትናም ሁለት ጦርነቶችን ያየች ሲሆን፣ የ16 ዓመት ልጅ እያለች አገሯ ከፈረንሳይ ነጻነቷን እንድታገኝ ታግላለች።
በሕክምና የተመረቀች ሲሆን፣ የክሊኒክ ኃላፊ፣ የጦርነት ዘጋቢ፣ ለቬትናም ቴሌቪዥን የፊልም ዳይሬክተር በመሆን ያገለገለች ሲሆን፣ እንዲሁም የሳይጎንን ታሪካዊ ውድቀት ማየት ችላላች።
በ62 ዓመቷ ጡረታ ከመውጣት ይልቅ፣በሆ ቺ ሚኒ ከተማ የግል ከሆኑ ጋለሪዎች መካከል አንዱ የሆነውን ሎተስን መስርታ የቬትናማውያን ጥበብ ሥራ ዓለም እንዲያየው አድርጋለች። የአገሯ አርቲስቶች ዝናቸው በመላው ዓለም እንዲናኝ የበኩሏን አድርጋለች።
ደራሲ እና ተርጓሚ
በኢራን ታዋቂ ከሆኑ ደራሲዎች መካከል አንዷየሆነችው ሻህርኑሽ ፓርሲፑር፣ በሥራዎቿ ነውር የተባሉ ጉዳዮች ላይ፣ እንደ የሴቶች ጭቆና፣ በአባዊ ሥርዓት ላይ ማመጽ የመሳሰሉት ላይ ታተኩራለች።
የልብ ወለድ ደራሲ በመሆን ሥራዋን የጀመረችው ፓርሲፑራ፣ በኢራን ብሔራዊ ቴሌቪዥን እና ሬድዮ ጣብያ ላይ ፕሮዲውሰር በመሆን ሰርታለች። ነገር ግን ከ1979ኙ አብዮት በፊት ሁለት ገጣሚ አክቲቭስቶች መገደላቸውን ተከትሎ ሥራዋን ለቅቃለች። ይህም ለመጀመርያ ጊዜ እንድትታሰር አድርጓታል።
ከአብዮቱ ጀምሮ፣ በኢራን ሥራዋ ታግዷል። 'ዉመን ዊዝአውት ሜን' በተባለው ሥራዋ ላይም በግልጽ ስለ ድንግልና በማንሳቷ ዳግም ታስራለች። ይህ መጽሐፍ በኋላ ላይ ከኢራን ውጪ ወደ ፊልም ተቀይሯል።
ፓርሲፑራ በተደጋጋሚ መታሰሯን ለስራዎቿ እንደ ግብዓት የምትጠቀም ሲሆን፣ ከ1994 ጀምሮ በአሜሪካ በስደት ትኖራለች።
የረዥም ርቀት ሯጭ
ትውልደ ኬንያዊቷ የሮማንያ የኦሎምፒክ አትሌት ጆአን ኬሊሞ፣ በረዥም ርቀት ሩጫ ስኬቷ የተነሳ ስሟ በደማቁ ተጽፏል። በዚህ ዓመትም በአውሮፓ ሻምፒዮንሺፕ የነሃስ ሜዳሊያ አግኝታለች።
ከስፖርት ባሻገር ደግሞ የጾታዊ ጥቃት ደረሶባት የሚያውቅ በመሆኑ፣ ከራሷ ታሪክ በመነሳት አትሌቶች እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች እንደሚደርሱባቸው ለማሳየት ትሰራለች።
እ.ኤ.አ. በ2021 የዓለም ሪከርድ ባለቤት የነበረችው ኬንያዊቷ አትሌት አግነስ ቲሮፕ ከተገደለች በኋላ ‘ቲሮፕስ ኤንጅልስ’ የተባለ ድርጅት ከሌሎች ኬንያውያን ጋር በመሆን በማቋቋም ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ላይ በተለያዩ ተግባራት ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና ለመከላከል ትሰራለች።
ድርጅቱ በዚህ ዓመት የኦሎምፒክ ሯጭ ሬቤካ ቼፕቴጊ በቀድሞ አጋሯ ከተገደለች በኋላ፣ በኬንያ ሴትን ልጅ መግደል ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።
እውነተኛ ለውጥ የሚጀምረው፣ ሕመማችን የታሪካችን መጨረሻ ሳይሆን የትልቅ ነገር መጀመሪያ መሆኑን ስንወስን ነው ብዬ አምናለሁ።
ጆአን ኬሊሞ ሜሊ
ሙዚቀኛ
በላቲን የሙዚቃ መድረክ ላይ ታዋቂ አቀንቃኝ እና የሙዚቃ ደራሲ የሆነችው ጓቲማላዊቷ ጋቢ ሞሬኖ፣ በ2024 በምርጥ የላቲን ፖፕ አልበም ግራሚ ተሸልማለች።
በሁለት ቋንቋዎች ሙዚቃ የምታቀናብረው እና ተጽዕኖዋን ከአሜሪካና የሶል እና ላቲን ባህላዊ ዘውግ የቀዳችው ሞሬኖ፣ ሙዚቃዋ እና አዚያዚያሟ ቱባ ባህሏን ያንጸባርቃል።
ሞሬኖ ለዩኒሴፍ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር በመሆን ስለ ሕጻናት መብቶች ለመሟገት የመጀመርያዋ ጓቲማላዊት ነች።
በቅርቡ 2.7 ሚሊዮን ወንዶች እና ሴቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ በሆኑባት አገር፣ ጥራት ያላቸው የመማርያ ቁሳቁሶች ተደራሽነት እንዲኖር ዘመቻ ጀምራለች።
አርቲስት እና የአየር ንብረት ተሟጋች
የአየር ንብረት ፍትህ ተሟጋች፣ ሙዚቀኛ እና የፊልም ባለሙያ የሆነችው ኢና ሞጃ፣ የሴት ልጅ ግርዛትን ከመቃወም እስከ ዘላቂነት ስላለው የአየር ንብረት ጥበቃ በመሟገት በርካታ ተግዳሮቶችን የተጋፈጠች ሴት ናት።
አፍሪካ በሰሀራ በረሃ፣ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ 12 አገራትን በሚያካልለው ሳህል አካባቢ፣ ያለውን የበረሃ መስፋፋት ለመግታት እና የተጎዱ መልክዓ ምድሮችን መልሶ ለማልማት የምታደርገውን ጥረት የሚያሳየው 'ዘ ግሬት ግሪን ዎል' የተሰኘ ፊልምን ፕሮዲውስ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በትወናም ተሳትፋለች።
የተባበሩት መንግሥታት በረሃማነትን መከላከል የበጎ ፈቃድ አምባሳደር የሆነችው ሞጃ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱ ማኅበረሰቦች ድምጽ ለመሆን ትጥራለች።
ቴክኖሎጂን እና ጌሚንግን ለበጎ ተጽዕኖ ለመጠቀም የሚሰራው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፣ኮድ ግሪን፣ መስራቾች መካከል አንዷ ናት።
ጥንካሬ ማለት የሴቶች እና ልጃገረዶች የለውጥ መፍትሄዎችን የመምራት ችሎታን ማሳደግ ነው።
ኢና ሞጃ
ድምጻዊ
ድምጻዊቷ እና የሙዚቃ ደራሲዋ ሬይ በዚህ ዓመት በብሪት አዋርድ ከተመረጠችባቸው ሰባት ዘርፎች በስድስቱ በማሸነፍ ታሪክ የሰራች ሲሆን፣ የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ደራሲ የሚለውን ዘርፍ በማሸነፍ ደግሞ የመጀመርያዋ ሴት ሆናለች።
በ2021 ሬይ በማኅበራዊ ሚድያዋ ላይ ከሙዚቃ አሳታሚ እና አከፋፋይዋ፣ ፖሊዶር፣ ጋር የመጀመርያዋን አልበም ለሕዝብ ለማድረስ ለሰባት ዓመታት ትግል ማድረጓን ገልጻ ነበር።
በ2023 'ማይ 21ስት ሴንቸሪ ብሉዝ' የተሰኘ አልበሟን በግሏ ለሕዝብ የለቀቀች ሲሆን፣ በሙዚቃ ባለሙያዎች እና በአድናቂዎቿ ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶላታል።
በሙዚቃው ዓለም እና ከዚያም ውጪ ያሉባትን ተግዳሮቶች ጾታዊ ትንኮሳ፣ የአደንዛዥ ዕጽ መጠቀም፣ ለሙዚቃ ደራሲዎች ፍትሀዊ ክፍያ እና ስለተክለ ሰውነቷ አብዝቶ በመጨነቅ ስለሚመጣ የአእምሮ ጤና ችግር በግልጽ ትናገራለች።
ተዋናይት
ተዋናይት ሄንድ ሳብሪ በአረብ ሲኒማ ውስጥ በጣም ታዋቂ ከሆኑ ሴቶች መካከል አንዷ ነች። ‘ዘ ሳይለንስስ ኦፍ ዘ ፓላስ’ (1994) የተሰኘው ፊልሟ በቱኒዚያ ያሉ ሴቶች የሚደርስባቸውን ወሲባዊ እና ማህበራዊ ብዝበዛ ያሳያል።
በ2019 የቬኒስ ፊልም ፌስቲቫል ላይ የመጀመርያዋ አረብ ሴት ዳኛ በመሆን አገልግላለች።
በቅርቡ በ2024 የኦስካር ሽልማት ላይ ከቱኒዚያ ለምርጥ ዘጋቢ ፊልም በተመረጠው 'ኦልፋስ ዶውተርስ' ላይ ተውናለች።
በሕዳር ወር ላይ ሳብሪ ከተባበሩት መንግሥታት የበጎ ፈቃድ አምባሳደርነቷ በጋዛ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀምን በመቃወም ለቅቃለች።
ስለ መኖር ብቻ አይደለም፤ በትግል ውስጥ ሕመምን ወደ ተግባር መለወጥ ጨምሮ . . . መልሶ መገንባት እና ዓላማ መፈለግ አለበት።
ሄንድ ሳብሪ
ተዋናይት
የሆሊውድ ተዋናይቷ ሻሮን ስቶን፣ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በፊልም ላይ እና ከዚያ ውጪ በርካታ ነገሮችን ሰርታለች።
በ1990ዎቹ ወደ ዝና የመጣችው ተዋናይቷ ቤዚክ ኢንስቲክት፣ ቶታል ሪኮል እና ካሲኖ የተሰኙ ፊልሞች ላይ የተወነች ሲሆን፣ በዚህም ጎልደን ግሎብን አሸንፋለች፤ ለኦስካር ታጭታለች።
በስኬት ከታጀበው የትወና ሕይወቷ ጎን ለጎን፣ ስቶን በርካታ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ላይ የምትሳተፍ ሲሆን፣ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ሰዎችን በመደገፍ ረገድ ላደረገችው አስተዋጽኦም እውቅና ተሰጥቷታል።
ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ፣ ስኬቷ በጎልደን ግሎብ ኢንተርናሽናል አዋርድ ላይ እውቅና ተሰጥቶታል።
ጥንካሬ ምርጫ ነው። አካሄድን መምረጥ ያስፈልጋል። ጉዳትን ወይንም ደስታን ልትመርጭ ትችያለሽ።
ሻሮን ስቶን
ድምጻዊ እና አቀናባሪ
የአፍጋኒስታን ሴቶች ድምጽ ከአደባባይ ሕይወት ተሰርዞ በነበረበት ወቅት፣ ድምጻዊ ኤላሃ ሶሮር ጭቆናን ለመታገል እና የብርታት መልዕክት ለማስተላለፍ 'ናን፣ ካር፣ አዛዲ' (ዳቦ፣ ሥራ፣ ነጻነት) የተሰኘውን ታዋቂ ዘፈኗን ጻፈች።
ዘፈኑ በአልቤኒያ በተካሄደው የጥቅምቱ የአፍጋን ሴቶች ጉባኤ ላይ ተለቀቀ።
በፊልም፣ ቲያትር እና ሙዚቃ ውስጥ ተሳትፎ ያላት እና ተሸላሚዋ አርቲስት ብዙ ጊዜ መድረክዋን ለሴቶች መብት ለመሟገት ትጠቀምበታለች።
በቁጥር አነስተኛ ከሆኑት የሀዛራ ብሄር የተገኘችው ሶሮር፣ በ2009 በተካሄደ የተሰጥኦ ውድደር ላይ ነው ከሕዝብ ጋር የተዋወቀችው። ሙዚቀኛ ለመሆን በመወሰኗ የተነሳ አመጽ የተቀላቀለበት ተቃውሞ ከገጠማት ወዲህ በ2010 አገሯን ለቅቃ ተሰድዳለች።
የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጅ እና ሞዴል
በዚህ ዓመት ማዲሰን ቴልቪን ‘አሲዩም ዛት አይ ካን’ ለተሰኘው ቅስቀሳ የሰራችው ቪዲዮ በመላው ዓለም በሚሊዮኖች ዘንድ መታየት ብቻ ሳይሆን፣ ዳውን ሲንድሮም ያለባቸው ሰዎች ላይ ያለውን ኢፍትሀዊነት ያፈራረሰ ጭምር ነበር።
የግንዛቤ ማስጨበጫው ቪድዮ በአጠቃላይ 150 ሚሊዮን ሰዎች ያዩት ሲሆን፣ ላመጣው በጎ ተጽዕኖም በካናስ ላዮንስ ፌስቲቫል ላይ የጎልድ ላዮን ታዋቂ ሽልማትን አግኝቷል።
ተዋናይት እና ሞዴል ቴቭሊን በኒውዮርክ ፋሽን ላይ የተሳተፈች ሲሆን፣ በክሊንተን ግሎባል ኢኒሼቲቭ ላይ በመገኘትም ስለ አቃፊነት ንግግር አድርጋለች።በተጨማሪም የኩዊንሲ ጆንስን ልዩ ሽልማትን ተቀብላለች።
ለተለያዩ ሽልማቶች የታጨውን 'ሁ ዱ ዩ ቲንክ አይ አም?' የመዝናኛ ዝግጅት እንዲሁም '21 ኩዌስችንስ' ፖድካስት ታቀርባለች።
ጥንካሬ ማለት የተሳሳተ ግምት ሲሰጠኝ ወይም ሆን ተብሎ እድሎች ሲያልፉኝ ወይም ዝቅ ተደርጌ ስገመት ተስፋ አለመቁረጥ ነው. . . ለማምንበት ነገር መቆም እና በራሴ እና በማኅበረሰቤ ተስፋ አለመቁረጥ ነው።
ማዲሰን ቴቭሊን
የአፍሮ ፖፕ ሙዚቀኛ
ድምጻዊዋና የሙዚቃ ደራሲዋ ኖኤላ ዊያላ ናዋዴይ በመድረክ ስሟ ዊያላ (በሲሳላ ቋንቋ "አድራጊ" ማለት ነው) በሚል የበለጠ ትታወቃለች።
በፋሽን ምርጫዋ እና በምትከተለው ልዩ ዘይቤ የምትታወቀው አርቲስቷ፣ በሰሜን ጋና የሚገኘውን የትውልድ አካባቢዋን ወግ እና ባህል ለማሳየት የመድረክ ልብሶቿን እና ጌጣ ጌጧን ራሷ ትሰራለች።
ብዙዎቹ የዘፈኗ ግጥሞች አፍሪካውያን ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ብዝበዛዎች እንዲታዩ አድርገዋል። ዊያላ ከተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች እና ከጋና ባለስልጣናት ጋር ያለ እድሜ ጋብቻን ለመዋጋት በቅርበት ሰርታለች።
በትውልድ ከተማዋ ፉንሲ ውስጥ ሥራ እና የፈጠራ ሥራን ለማስተዋወቅ የኪነጥበብ ማዕከል፣ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ እና ሬስቶራንት ገንብታለች።
የጂምናስቲክ ስፖርተኛ
የጂምናስቲክ ስፖርተኛዋ ሬቤካ ስድስት ሜዳሊያዎችን በማግኘት በብራዚል ከፍተኛ ቁጥር ሜዳሊያ ካገኙ አትሌቶች መካከል ግንባር ቀደሟ ናት ። በተጨማሪም ዘጠኝ የዓለም ሻምፒዮና ድሎችም በስሟ ተመዝግበዋል።
በፓሪስ 2024 ስመ ጥሯን የአሜሪካ ጂምናስት፣ሲሞን ቢሊስን፣ በማሸነፍ ወርቅ አግኝታለች። በሜዳልያ ስርዓቱ ወቅት ቢሊስ እና ሌላዋ አሜሪካዊ ጂምናስት ጆርዳን ቺልስ ለብራዚላዊቷ ክብራቸውን በማጎንበስ ገልጠዋል። ይህም በዘንድሮው ኦሎምፒክ ላይ የታየ እና ብዙዎች የተጋሩት ሆኗል።
ከስምንት ወንድም እና እህቶች መካከል የተገኘቸው አንድራዴ፣ ከ10 ዓመቷ ጀምሮ እናቷ የሰው ቤት እያጸዳች ለስልጠናዋ ትከፍልላት ነበር።
ታዋቂነቷ በርካታ ጉዳቶችን ተከትሎ የመጣ ሲሆን፣ ምንጊዜም የአእምሮ ጤናን ማስቀደም እንደሚገባ በግልጽ ትናገራለች።
ጠንካራ መሆን ማለት እኛ ላይ ከሚደርሰው አንጻር፣ ነገሮችን የምንይዝበት መንገድ ሲሆን፤ እንዲሁም ነገሮች ቢበላሹ እንኳ በጎ ጎኑን ለማየት የቡድን አባላቶቼን መደገፍን ይጨምራል።
ሬቤካ አንድራዴ
ቀስት ወርዋሪ
በ2019 በቀድሞ ፍቅረኛዋ በቤቷ ሳለች ጥቃት የደረሰባት ትሬሲ ኦቶ፣ ከደረቷ በታች መንቀሳቀስ እንዳትችል፣ የግራ ዓይኗ እንዲጠፋ አድርጎታል። ከዚህ ጥቃት በፊት የአካል ብቃት ሞዴል ለመሆን ታልም የነበረችው ትሬሲ፣ ዳግም ሕይወቷን ለመቀጠል ቁርጠኛ ሆናለች።
በመጋቢት 2021 ኦቶ ከዚህ በፊት ሞክራው የማታውቀውን ቀስት አነሳች። ለመጀመርያ ጊዜ የወረወረችው ቀስት ዒላማውን ከመታ ወዲህ በስፖርቱ ተማርካ ቀረች።
በዚህ ዓመት፣ ኦቶ፣ለመጀመርያ ጊዜ በፓሪስ ፓራሊምፒክስ ላይ ተሳትፋለች። ከአካል ጉዳቷ የተነሳ ቀስቱን ለመወርወር አፏን ትጠቀማለች።
ኦቶ ለአምስት ዓመታት ያህል ከራሷ ልምድ በመነሳት ከቤት ውስጥ ጥቃት ስለመውጣት ታስተምራለች፤ ትቀሰቅሳለች።
የሮክ ባንድ ሙዚቀኛ
ፊሪዳ ማርስያ ኩሪኒያ፣ ቤሰርቦት በተሰኘው እና ሁሉም አባላቱ ሂጃብ የሚለብሱ ሴቶች በሆኑበት የሮክ ባንድ ውስጥ መሪ ድምፃዊ እና ጊታሪስት በመሆኗ ፈታኝ የሆኑ ሥርዓተ ፆታ እና የሃይማኖት መመዘኛዎች ምቾት ይሰጧታል።
በኢንዶኔዥያ ውስጥ በሰፊው ከሚነገሩ ቋንቋዎች መካከል በእንግሊዘኛ እና በሰንዳኒዝ ስትዘፍን ግጥሞቿ በወንዶች የበላይነት በተያዘው ሥርዓት ላይ ያላትን ቅሬታ ይገልጻሉ።
የሙዚቃው ሀሳብ እና የሮክ ሙዚቃ በአንድነት በመቅረባቸው የተነሳ ወግ አጥባቂ ከሆኑ ሙስሊሞች ተቃውሞ ገጥሟታል።
ይኹን እንጂ ቡድኑ በምዕራብ ጃቫ በምትገኘው ጋሩት ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የዛሬ 10 ዓመት ከተመሠረተ ወዲህ ረዥም ርቀት ተጉዟል።በዚህ ዓመት በግላስቶንበሪ ሥራዎቻቸውን በማቅረብ በፌስቲቫሉ የ54 ዓመት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የኢንዶኔዢያ ባንድ ሆነዋል።
በኦሎምፒክ የአካል ጉዳተኛ ቴኳንዶ ተወዳዳሪ
ዛኪያ ክዳዳዲ በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ ሜዳሊያ በማሸነፍ የመጀመርያዋ የፓራሊምፒክ የስደተኞች ቡድን በመሆን ታሪክ ሰርታለች።
አንድ እጅ ብቻ ይዛ የተወለደችው አትሌቷ፣ በተወለደችበት በምዕራብ አፍጋኒስታን በሚገኘው ሄራት በሚገኝ ጂም በ11 ዓመቷ በድብቅ የቴኳንዶ ልምምድ ማድረግ ጀመረች።
በ2021 ታሊባን ወደ ስልጣን መመለሱን ተከትሎ በቶኪዮ ፓራሊምፒክስ ላይ እንዳትሳተፍ ተከልክላ ነበር።
ነገር ግን ከዓለም አቀፉ የፓራሊምፒክስ ኮሚቲ እና ከፈረንሳይ ድጋፍ በማግኘቷ፣ ከአፍጋኒስታን ወጥታ ታሊባን ስልጣን ከያዘ ወዲህ በዓለም መድረክ ላይ አፍጋኒስታንን የወከለች የመጀመርያዋ ስፖርተኛ ለመሆን ችላለች።
እኔ ለኦሎምፒክ ሜዳልያ ያደረግኩት ጉዞ የአፍጋኒስታን ሴቶችን፣ የስደተኛ ሴቶችን፣የእያንዳንዷን ሴት ጥንካሬ ያሳያል። ከአሁን በኋላም ሴት ልጅ የማትችለው ነገር እንደሌለ ማሳየት እንቀጥላለኝ።
ዛኪያ ኩዳዳዲ
ድምጻዊ እና የሙዚቃ ደራሲ
የፓኪስታን ሙዚቃ ፈርጥ የሆነችው ሀዲቃ ኪአኒ በስርቅርቅ ድምጿ እና በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ ባላት ተሳትፎ ትታወቃለች።
በ1990ዎቹ ወደ እውቅና ማማ የመጣች ሲሆን፣ በደቡብ እስያ ሴት ሙዚቀኞች መድረክ ገናና ነች። እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ልማት ፕሮግራም የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ነች።
በ2022 በፓኪስታን በደረሰው አስከፊ የጎርፍ አደጋ ወቅት በባሎቺስታን እና በደቡብ ቡንጃብ ግዛቶች የተጎዱትን ለመርዳት አንድ ፕሮጀክት ጀምራ ነበር።
ማኅበረሰቡ የተፈናቀሉ ዜጎቸን እንዲረዳ የጠየቀችው ኪአኒ፣ በፕሮጀክቷ 370 ቤቶችን መገንባቷን እንዲሁም ጉዳት በደረሰበት አካባቢ ሌሎች ነገሮችን አሟልታለች።
ኮሜዲያን
ናኦሚ ዋታናቤ በጃፓን ዝነኛ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆኗን ተጠቅማ ለወጣት ሴት ኮሜዲያን መንገዶችን ታመላክታለች።
በጃፓን በወንዶች በስፋት በተያዘው የኮሜዲ ዘርፍ ውስጥ ዋና ገፀ-ባህሪን ወክላ በመጫወት እንዲሁም ተወዳጅ አጫጭር ተውኔቶችን በማቅረብ እንቅፋቶችን ጥሳ መውጣት ችላለች።
ዋታናቤ በጃፓን ከተክለ ሰውነት ጋር ተያይዞ የሚደርሱ ማግለሎችን ለመለወጥ የሚሠራው ‘ፖቻካዋኢ’ (ቆንጆ ድንቡሽቡሽ) የተባለው እንቅስቃሴ ላይ ትሳተፋለች። በጃፓን ከቀዳሚዎቹ መካከል አንዱ የሆነ እና ለወፍራም ሰዎች ልብሶችን የሚያቀርብ ድርጅት ከፍታለች።
በጃፓን ቴሌቪዥን እና ፊልም ላይ ትልቅ እውቅና ከተጎናጸፈች በኋላ፣ ወደ አሜሪካ በማቅናት ዓለም አቀፍ የኮሜዲ መድረክ ለማግኘት እየሠራች ትገኛለች።
ሁሌም የማስበው፣ እንዴት ነው ተቋቁመው የሚዘልቁት? እያልኩ ነው። 'አትወዱኝም፣ምንም አይደለም። እባካችሁ አንድ ዓመት ስጡኝ እና ምናልባት ሀሳባችሁን እለውጠው ይሆናል' ሁሌም ያለኝ አስተሳሰብ ይሄ ነው።
ናኦሚ ዋታናቤ
የፊልም ዳይሬክተር
የኦስካር አሸናፊ የሆነችው የፊልም ዳይሬክተር እና ደራሲ ክሎዊ ዛኦ፣ የአካዳሚውን የምርጥ ዳይሬክተር ሽልማት በማሸነፍ ነጭ ካልሆኑ ሴቶች የመጀመሪያዋ እና በታሪክ ውስጥ ደግሞ ከሦስቱ ሴቶች መካከል አንዷ ናት።
ቤይጂንግ ውስጥ የተወለደችው ዛኦ በዩኬ እና በአሜሪካ ኖራለች። ራሷን በተለያየ ስፍራ እየተንቀሳቀሰ የሚኖር ስትል የምትገልጸው ዛኦ፣ ተሸላሚ የሆነው ‘ኖማድላንድ’ (2020) የተሰኘው ፊልም ይህንኑ ጭብጥ የሚያሳይ ነው።
ዛኦ መጀመሪያ አካባቢ ከሰራቻቸው እና ስለ ቀደምት ማኅበረሰቦች ከሚያትቱት ፊልሞቿ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜዎቹ በርካታ ተዋናዮችን ካሳተፉት የማርቭል ዩኒቨርስ ፊልሞቿ ድረስ፣ እንደ ሰው ስለሚያስተሳስሩን ነገሮች ማሳየት የበለጠ ያስደስታታል።
በዚህ ዓመት በ2025 ይለቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው እና መነሻ ሀሳቡን የማጊ ኦ’ፋሬል ልቦለድ ላይ ያደረገውን 'ሃምኔት'ን እያዘጋጀች ነው።
እየሠራንበት ያለውን የኢንዱስትሪ መዋቅር ካልቀየርን ዋጋ እንዲኖረን ከወንዶች ጋር መመሳሰል አለብን እያልን ነው። ጉልበታችን ያለው እዚያ ላይ አይመስለኝም።
ክሎዊ ዛዎ
የጠረጴዛ ቴኒስ ተጫዋች
የቻይና እና ቺሊ ዝርያ ያላት የጠረጴዛ ቴኒስ ተጫዋቿ ዢዪንግ ዜንግ ወይም ታኒያ በ58 ዓመቷ በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ ተሳትፋለች።
ይህ ለረዥም ጊዜ ስትናፍቀው የነበረ ነገር ነው። እናቷ አሰልጣኝ በመሆናቸው የተነሳ ወደ ስፖርቱ የገባችው በለጋ እድሜዋ፣ የ12 ዓመት ታዳጊ ሳለች ነበር። በወቅቱ ለቻይና ብሄራዊ ቡድን ብቁ የነበረች ቢሆንም፣ ወደ ቺሊ በመሄዷ ስፖርቱን ለ30 ዓመታት ትታ በሌላ ጉዳዮቿ ላይ አተኩራ ቆይታለች።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ታኒያ ዜንግን ወደ ጠረጴዛ ቴኒስ እንድትመለስ አድርጓታል።
በአውሮፓውያኑ 2023 በቺሊ፣ አገሯን በደቡብ አሜሪካ ሻምፒዮና እና በፓን አሜሪካ ጨዋታዎች በመወከል፣ ‘የሕይወት ዘመን ሕልሟ’ የሆነው ለኦሎምፒክ ለመሳተፍ የሚያስፈልገውን መስፈርት በማሟላት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰች ሴት ነበረች።
በተኩስ የኦሎምፒክ ተወዳዳሪ
ኪም ዬጂን በዚህ ዓመት የዓለም ሕዝብ እንዲያያት ያደረገው ያላት ሰብእና እና የስፖርት ስኬት ነው
በሽጉጥ ተኩስ ለመጀመርያ ጊዜ በኦሎምፒክ የተሳተፈችው ዬጂን በ10 ሜትር ተኩስ የነሐስ ሜዳልያ አግኝታለች። ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ በ25 ሜትር የሴቶች ሽጉጥ ተኩስ የዓለም ክብረወሰንን አስመዝግባለች።
በማኅበራዊ ሚድያ ቪዲዮዎቿ በበርካታ ሰዎች የታዩ እና የተጋሩ ሲሆን፣ ክህሎቷን ማድነቅ ብቻ ሳይሆን ሰብዕናዋን፣ ምንም ነገር የማያናጥበው ትኩረቷን፣ የምትጠቀመው መነጽር ሁሉ በርካቶችን የሳቡ ነበሩ።
ኪም ዬጂ ከእናትነት ጋር ተያይዞ ስለሚመጣ ኃላፊነት በግልጽ ትናገራለች። ከስድስት ዓመት ልጇ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ በሚል ከስፖርት የተወሰነ ጊዜ ራሷን አግልላ ነበር።
በስፖርት ውስጥ ጥንካሬያችንን፣ የቡድን ሥራ እና ቁርጠኝነትን እናሳያለን። በእኔ አተያይ ግን ይህ ከጨዋታ ሜዳ ውጪ አልፎ በርካቶችን ለማኅበራዊ ለውጥ የሚያነሳሳ ነው።
ኪም ዬጂ
የተለያዩ የሩጫ ውድድሮች አትሌት
በዓለም ሻምፒዮና 20፣ በኦሊምፒክ ደግሞ 11 ሜዳሊያዎችን በስሟ ያስመዘገበችው አሊሰን ፌሊክስ፣ ታሪክ ስሟን በደማቁ የጻፈው በተለያዩ የሩጫ ውድድሮች ተሳትፋ ነው።
በእርግዝና ወቅት ካጋጠማት የጤና እክል (ከፍተኛ የደም ግፊት) የተነሳ ሴት ልጇን የወለደችው ያለ ጊዜዋ ነበር። ከዚያ በኋላ ለሚወልዱ እናቶች ጤና መብት ተሟጋች ሆነች። አሁን በአሜሪካ ውስጥ ላሉ ጥቁር ሴቶች የእናቶች ጤና እንክብካቤን ለማስፋፋት ከሜሊንዳ ፍሬንች ጌትስ የ20 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አግኝታለች።
ሩጫ ያቆመችው ይህች አትሌት፣ በፓሪስ 2024 ጨዋታዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ መንደር የሕፃናት ማቆያ እንዲኖር አስተዋፅዖ አድርጋለች።
በዚህ ዓመትም የዓለም አቀፉን ኦሊምፒክ ኮሚቴ የአትሌቶች ኮሚሽንን እንድትቀላቀል የተመረጠች ሲሆን፣ በተጨማሪም በሴቶች ስፖርት ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ የራሷን የስፖርት አስተዳደር ኩባንያ አቋቋማለች።
አንድን ነገር የመቋቋም ብቃት ጥንካሬን የመፈለግ፣ ከባድ ሁኔታዎችን ፊት ለፊት የመጋፈጥ ውበት ነው፤ እንዲሁም ወደፊት ለመራመድ እያንዳንዱን እንቅፋት እንደ ነዳጅ መጠቀምም ነው።
አሊሰን ፌሊክስ
ነጻ ትግል ተጋጣሚ
ሦስት ጊዜ የኦሊምፒክ አሸናፊ የሆነችው ቪኔሽ ፎጋት በሕንድ ውስጥ በርካታ ሜዳልያዎችን ካገኙ ስፖርተኞች መካከል አንዷ እና በስፖርት ውስጥ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ፆተኛ አመለካከት አጥብቃ የምትተች ነች። በዓለም ሻምፒዮና፣ በኮመንዌልዝ እና በእስያ ጨዋታዎች ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
ፎጋት በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በነጻ ትግል በኦሊምፒክ ለፍጻሜ የደረሰች ሕንዳዊት ሆናለች። ነገር ግን በክብደቷ የተነሳ ከውድድር ውጪ ሆናለች። በኋላም ከስፖርት ራሷን አግልላ ወደ ፖለቲካው ጠቅልላ ገብታለች።
ስለ ሥርዓተ-ፆታ የተዛቡ አመለካከቶች በድፍረት የምትቃወመው ፎጋት፣ የሕንድ ነጻ ትግል ስፖርተኞች የፌደሬሽኑን ኃላፊ፣ ብሪጅ ቡሻን ሲንግ፣ሴት አትሌቶች ላይ ፆታዊ ትንኮሳ ያደርሳል በሚል ለወራት የዘለቀው ተቃውሞ ሲያካሄዱ፣ ምንም እንኳ እርሱ ቢያስተባብልም፣ ግንባር ቀደም በመሆን ተሳትፋለች።
ፖሊስ ፎጋትን እና ሌሎችን በቁጥጥር ስር ሲያውል ተቃውሞው የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት አገኘ።
ለእኔ ነገሮችን መቋቋም ማለት በሥራ ቦታ አስቀያሚ ቀን ካሳለፉ በኋላ ለራስ ክብር እና ሞገስ የመስጠት ችሎታ ነው ።
ቪኔሽ ፎጋት
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር
በዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ በመያዝ፣ አንጄላ ራይነር በሐምሌ ወር በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነች።
በስቶክፖርት ተወልዳ ያደገችው ራይነር ከልጅነቷ ጀምሮ እናቷን ትንከባከብ የነበረች ሲሆን፣ በ16 ዓመቷ በማርገዟ ትምህርቷን አቋርጣለች። በአካባቢው ምክር ቤት በማኅበራዊ ክብካቤ ውስጥ የሠራችው ራይነር፣ የሠራተኛ ማኅበር ተወካይ በመሆን ወደ ሥልጣን ማማ መውጣት ችላለች።
ራይነር የሌበር ፓርቲ ተወካይ በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ለፓርላማ የተመረጠችው እኤአ በ2015 ነበር። በወቅቱ ከምርጫ ክልሏ የመጀመሪያዋ ሴት ተወካይ የነበረች ሲሆን፣ በኋላም በምክር ቤት ውስጥ የሴቶች እና እኩልነት ትይዩ ካቢኔ ሚኒስትር (ሻዶ ሚኒስትር) በመሆን ሌሎች ኃላፊነቶችንም ደርባ ሠርታለች።
በአሁኑ ወቅት የቤቶች፣ የማኅበረሰብ እና የአካባቢ አስተዳደር ፀሐፊ በመሆን እያገለገለች ነው።
የተመሳሳይ ጾታ አፍቃርያን መብቶች ተሟጋች
ታይላንድ በዚህ ዓመት የጋብቻ እኩልነት ሕግን ከፈረመች በኋላ በደቡብ ምስራቅ እስያ የተመሳሳይ ጾታ ጥምረትን እውቅና የሰጠች የመጀመርያ አገር ሆናለች። አን 'ዋዶ' ቹምፖርን ይህንን ለማክበር ምክንያት አላት።
ሕጉ በፓርላማ እንዲያልፍ ግንባር ቀደም ሆነ ስትቀሰቅስ የነበረ ሲሆን፣ በሕዝብ ተወካዮችም ሆነ በሴኔት ውስጥ የሕግ ማሻሻያ ኮሚሽነር ሆና አገልግላለች።
ቹማፖርን ለሰብዓዊ መብት፣ ለተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች እና የቤተሰብ መብት ለአስርታት ስትታገል የነበረች ሲሆን፣ የባንኮግ ፕራይድ መስራች ከሆኑት መካከል አንዷ ናት።
የታይላንድ ወጣቶች በ2020 ለተቃውሞ አደባባይ በወጡበት ወቅት፣ ከሴቶች መብት ጋር በተያያዘ ግንባር ቀደም የነበረች ሲሆን በዚህም የተነሳ ስምንት ክሶች ተከፍቶባታል።
ጠበቃ
በሕግ እና ፍትህ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ያላት ሩት ሎፔዝ፣ በማዕከላዊ አሜሪካ ዲሞክራሲን ለማሻሻል የሚሰራው ክሪስቶሶል የተሰኘ ድርጅት ዋና የሕግ ባለሙያ ናት።
ዋነኛ ትኩረቷም በኤል ሳልቫዶር ፀረ ሙስና፣የምርጫ ሕግ እና ሰብዓዊ መብቶች መከላከል ናቸው።
የአገሪቱ መንግሥት እና ተቋማት ቀንደኛ ተቺ ስትሆን፣ በማኅበራዊ ሚድያ ላይ በሕዝብ ቅኝት የሚደረግበት የፖለቲካ ግልጸኝነት እና ለሕዝብ ተጠያቂነት እንዲኖር ትወተውታለች።
ሥራዋ የበለጠ እይታ ውስጥ የገባው ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ የኤልሳልቫዶር ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬሌ ዳግም ከተመረጡ በኋላ ነው። ቡኬሌ ወንጀለኞች ላይ በወሰዱት እርምጃ ተቀባይነት ቢያገኙም ራሳቸውን " የዓለማችን ምርጡ አምባገነን ነኝ" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
የሰላም ኖቤል ሽልማት ሎሬት
ናድያ ሙራድ በአውሮፓውያኑ 2014 ራሱን እስላማዊ መንግሥት (አይኤስ) ብሎ የሚጠራው ቡድን በኢራቅ ያዚዲዎች ላይ ከፈጸመው የዘር ማጥፋት ተርፋለች። አሁን ከፆታዊ ጥቃት ለተረፉ ግንባር ቀደም ተሟጋች ስትሆን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ ነች።
በአይኤስ ታጣቂዎች ተይዛ ለባርነት ተዳርጋ የነበረችው ናድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና ጥቃት ተፈጽሞባታል። ናድያ ከሦስት ወራት በኋላ አምልጣ የደረሰባትን ፈተና ለዓለም ያለመሸማቀቅ በመናገር ከግጭት ጋር በተያያዙ ወሲባዊ ጥቃቶች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እየሠራች ነው።
አይኤስን ተጠያቂ ለማድረግ ከሰብዓዊ መብት ጠበቃዋ አማል ክሉኒ ጋር ተጣምራለች፤ ማኅበረሰቦችን መልሶ ለመገንባት እና ከጥቃት የተረፉት ካሳ የሚያገኙበት ላይ ለመሥራት ደግሞ የናዲያ ኢኒሼቲቭን ጀምራለች።
የያዚዲ እልቂት ከተፈጸመ ከ10 ዓመታት በኋላ ናድያ ችግሮችን የመቋቋም ዓለም አቀፍ ምልክት ሆና ቀጥላለች።
ለእኩልነት እና ለፍትህ ለመታገል፣ እኔ ‘የመንፈስ ትጥቆች’ ስል የምጠራቸውን እውነት፣ ተስፋ እና ርህራሄ መጠቀም አለብን።
ናድያ ሙራድ
የሰብዓዊ መብት ጠበቃ
በቬንዙዌላ ካራከስ ወደሚገኝ የሕጻናት ሆስፒታል የሚመጡ በርካታ ታዳጊ ሕሙማን ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው እና በአንድ ወላጅ ብቻ ከሚመሩ ቤተሰቦች የተገኙ ናቸው።
በካትሪን ማርቲኔዝ የተመሰረተው፣ ፕሪፓራ ፋሚሊያ፣ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ልብስ፣ ሕክምና ቁሳቁሶች፣ ምግብ እና የስነልቡና ድጋፍ ይሰጣቸዋል።
እንደ ሰብአዊ መብት ጠበቃ፣ ማርቲኔዝ እና ቡድኗ በሆስፒታል ውስጥ በሕፃናት እና በሴቶች ተንከባካቢዎች ላይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጎጂዎችን ካሳ እንዲያገኙ ለማስቻል የሚያዩትን ነገር መዝግበው ይይዛሉ።
በቬንዙዌላ ባለው ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት የተነሳ፣ ፕሬፓ ፋሚሊያ ለሕጻናት እና ነፍሰጡር እናቶች የተመጣጠነ ምግብ እና ቫይታሚን ያለምንም ክፍያ የሚሰጥ ማዕከል ከፍቷል።
ፖለቲከኛ
የ22 ዓመቷ ሐና-ራዊቲ ማይፒ-ክላርክ በእድሜ ትንሿ የማኦሪ ተወላጅ፣ የኒው ዚላንድ ፓርላማ ተመራጭ ነች።
በመጀመርያ የፓርላማ ንግግሯ ወቅት፣ የማኦሪ ባህላዊ ውዝዋዜ የሆነው ሃካን በማሳየት፣ የነባር ሕዝቦች ውክልና እንዲጨምር ጠይቃለች። በቅርቡም አወዛጋቢ የሆነውን ሕግ በመቃወም በፓርላማ ውስጥ ሌላ ባሕላዊ ውዝዋዜ የመራች ሲሆን ስብሰባው እንዲቋረጥ ሆኗል።
ማይፒ-ክላርክ ለሞሪ ሕዝቦች መብቶች፣ ለባህል ጥበቃ እና የአካባቢ ጉዳዮች ትታገላለች። ስለ ማኦሪ የጨረቃ አቆጣጠር የሚያትተው የመጀመርያ መጽሐፏን በ17 ዓመቷ አሳትማለች።
በዚህ ዓመት የነባር ማኅበረሰብ ወጣቶች ድምጽን በፖለቲካ ውስጥ ለማጉላት ላደረገችው ጥረት የተከበረውን የ’ዋን ያንግ ወርልድ ፖለቲሽያን’ ሽልማት ተቀብላለች።
ሴቶች በአካባቢያቸው፣ በአገራቸው ወይንም ዓለም አቀፍ ፖለቲካዎች ውስጥ ባይጋበዙ እንኳ እንቅፋቶችን ጥሰው ገብተው መሳተፍ አለባቸው።
ሐና-ራዋሂቲ ማኢፒ-ክላርክ
የአይሪሽ ተጓዦች እንቅስቃሴ አክቲቪስት
ላቲሻ ማክክሩደን 20 ዓመቷ ቢሆንም ለአይሪሽ ተጓዥ ማኅበረሰቦች ጠንካራ ተከራካሪ በመሆን ራሷን ከፊት አስቀምጣለች።
የማኅበረሰቡ አባል በመሆኗ ተሰሚነቷን፣ በአየርላንድ ውስጥ ባሉ አናሳ ጎሳዎች ዙሪያ የሚደረጉ አሉታዊ ድርጊቶችን ለመዋጋት፣ እንዲሁም ከቤት ውስጥ ጥቃት እንደተረፈች አንዲት ሴት ደግሞ ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃትን ለመዋጋት ትጠቀምበታለች።
በጋልዌይ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪ የሆነችው ማክክሩደን የአይሪሽ ተጓዥ ንቅናቄ ብሄራዊ የወጣቶች መድረክ፣ የአየርላንድ ብሄራዊ የሴቶች ምክር ቤት እና የተጓዥ ድጋፍ ቡድን አባል በመሆን ታገለግላለች።
በአውሮፓውያኑ 2029 በሚደረገው የአካባቢ ምርጫ ለመወዳደር እና በአየርላንድ ለውጥ ለማምጣት ተስፋ አድርጋለች።
የማዕድን ባለሙያ
ኮንጓዊቷ አኒ ሲናንዱኩ ምዋንጌ በማዕድን ንግድ ውስጥ የተሰማራች ሴት ብቻ ሳትሆን፣ በማዕድን ማውጫው ከሚሰሩት ግማሽ ያህሉ ሴቶች በመሆናቸውም ጭምር በኢንዱስትሪው ውስጥ አድልዎ እና ጾታዊ ትንኮሳን ለመዋጋት ሕዝባዊ ንቅናቄን ትመራለች።
ብሔራዊ የሴቶች ማዕድን ትስስር (Renafem) መሪ ስትሆን፣ ራሷን እንደ ተራ ወይም እናት አለቃ ትቆጥራለች። ከዚህም ባሻገር ሴቶችን በማዕድን ማውጫ ቦታዎች ላይ ኃላፊ በማድረግ ከወንዶች ባልደረቦቻቸው የሚደርስባቸውን የወሲብ ብዝበዛ ለመከላከል ትሰራለች።
በዓለም ላይ ለኤሌትሪክ መኪና የሚያስፈልጉ እንደ ኮባልት እና ሌሎች ማዕድናት ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ የተነሳ፣ በሴቶች ሕይወት ላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በዘርፉ የሚታየውን የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመቀነስ ተስፋ ሰንቃለች።
ማሕበራዊ አክቲቪስት
በሕንድ ውስጥ ለድሆች መብት ተሟጋች የሆነችው አሩና ሮይ ከገጠር ማኀበረሰቦች ጋር በቀጥታ ለመሳተፍ በሚል የነበራትን መንግሥታዊ ሥራ ትታለች።
ማዝዶር ኪሳን ሻክቲ ሳንጋታን (MKSS) የተሰኘ ድርጅት መስራች ነች። ድርጅቱ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እና ፍትሀዊ የደሞዝ ክፍያ ላይ የሚታገል ሲሆን፣ በ2005 ዜጎች መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርጉበት ሕግ እንዲወጣ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
ሮይ ከአራት አስርት ዓመታት በላይ በዜጎች የሚመሩ ሥራዎች ላይ ግንባር ቀደም ሆና ተሳትፋለች። በዚህ ሥራዋም ብዙ ሽልማቶችን 'የእስያ የኖቤል ሽልማት' በመባል የሚታወቀውን ራሞን ማጋሳይን ጨምሮ አስገኝቶላታል።
የሕንድ ሴቶች ብሔራዊ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ስትሆን፣ በዚህ ዓመት የግል ማስታወሻዋን አሳትማለች።
በትልቁ ንድፍ ላይ የበለጠ ጊዜ ከማጥፋታችን የተነሳ፣ ብዙ ጊዜ ጎረቤታችን ያለውን ሕልም አናይም።
አሩና ሮይ
በግዳጅ ማምከንን ተሟጋች
ከሴሬብራል ፓልሲ ጋር የተወለደችው ዩሚ ሱዙኪ ከልጅነቷ ጀምሮ አድልዎ ይደርስባት ነበር። ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለች ማሕፀኗ በቀዶ ሕክምና እንዲወጣ ተደረገ።
በጃፓን እ.ኤ.አ. ከ1950ዎቹ እስከ 1990ዎቹ ድረስ እንደ ሱዙኪ ያሉ አንዳንድ አካል ጉዳተኞች በግዳጅ እንዲመክኑ የተደረጉት በወቅቱ በነበረው አግላይ የሥነ ተዋልዶ ሕግ (eugenics law) ምክንያት ሲሆን፣ ይህ ሕግ በ1996 ተሽሯል።
ሱዙኪ ከሌሎች 38 ሰዎች ጋር በመሆን መንግሥትን የከሰሱ ሲሆን ለዓመታት በፍርድ ቤት ክርክር ከተደረገ በኋላ አሸንፋለች። በሐምሌ ወር የጃፓን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድርጊቱ ኢሕገ መንግሥታዊ ነው በማለት መንግሥት ለተጎጂዎች ካሳ እንዲከፍል ወስኗል።
መንግሥት 16ሺህ 500 ሰዎች ከእውቅናቸው ውጪ እንዲመክኑ መደረጉን ይፋ አድርጓል።
የሕክምና ዶክተር እና የፖለቲካ አክቲቪስት
በመላው ፓኪስታን በባሎቺስታን አውራጃ በግዳጅ ደብዛቸው የሚጠፋ ሰዎችን በሚመለከት አደባባይ ወጥተው ሰልፍ ካደረጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች መካከል ማሀራንግ ባሎች አንዷ ናት።
ለፍትህ መጮህ የጀመረችው በ2009 አባቷ በጸጥታ አካላት ተወስደው ደብዛቸው ከጠፋ ከሁለት ዓመት በኋላ፣ ተደብድበው ሞተው ከተገኙ ወድያ ነው።
በ2023 መጨረሻ አካባቢ ባሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን ወደ ኢዝላማባንድ 1600 ኪሜ ጉዞ አድርገው የቤተሰብ አባላቶቻቸው ስላሉበት ሁኔታ መረጃ እንዲጠይቁ አድርጋለች። በዚህ ጉዞ ወቅት ሁለቴ በቁጥጥር ስር ውላለች።
በባሎቺስታን አውራጃ የሚኖሩ ሰልፈኞች፣ ዘመዶቻቸው በፓኪስታን የጸጥታ ኃይሎች፣ በግዛቲቱ ባለው የጸረ አማፂያን እንቅስቃሴ ምክንያት ተወስደው መገደላቸውን ይናገራሉ። በኢዝላማባድ የሚገኙ ባለስልጣናት ግን ይህንን ውንጀላ ያስተባብላሉ።
የሕክምና ዶክተሯ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ፣ ራሷ ባቋቋመችው እና 'ባሎች ያክጄቲ' (አንድነት) በተሰኘው ኮሚቴ አማካኝነት ወሳኝ አክቲቪስት ሆናለች።በሰብዓዊ መብት ላይ የምትሰራው ስራም በታይም መጽሔት እውቅና አግኝቷል።
በወሲብ ንግድ ላይ ለተሰማሩ መብት ተሟጋች
ሎርዴስ ባሬቱ ከበርካታ ዘመቻዎች ጀርባ ያለች ሴት ስትሆን፣ የሕይወት ዘመኗን ያሳለፈችው በብራዚል የሚገኙ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የተሻለ መብቶቻቸው እንዲከበርላቸው በመቀስቀስ ነው።
የአክቲቪዝም ስራዋን በአማዞን ክልል ቤሌም ዶ ፓራ የጀመረች ሲሆን፣ በ1980ዎቹ በላቲን አሜሪካ የመጀመርያው የሆነውን፣ የብራዚል ወሲብ ነጋዴዎች ጥምረትን ከሌሎች ጋር በመሆን መስርታለች።
አሁን በ80ዎቹ ውስጥ የምትገኘው ባሬቶ፣ ለአስርት ዓመታት ጥላቻን ስትታገል ኖራለች።
በአገሪቱ የኤችአይቪ መከላከል ፖሊሲዎች እንዲኖሩ በማድረግ ረገድ ቁልፍ የነበረች ሲሆን፣ በወርቅ ቁፋሮ ላይ የተሰማሩ ማኅበረሰቦች መካከል የኤችአይቪ ስርጭት እንዳይስፋፋ ታስተምር ነበር። በ2023 ግለ ታሪኳን አሳትማለች።
ታሪካችን አይታፈን፤ ዋጋ ይሰጠው። በዓለም ላይ ያለን ሴቶች ለማለም፣ ለማሳካት፣ ለማሰብ፣ ብሎም ማኅበረሰቡን ለመቀየር ያልተገደበ አቅም አለን።
ሎርዴስ ባሬቶ
የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ መሪ
ባለፈው መጋቢት ወር የዩኬ ወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ሆና ተመርጣለች። ኬሚ ባዴኖች የዩናይትድ ኪንግደም ዋና የፖለቲካ ፓርቲን በመምራት የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ሆናለች።
በአሁኑ ወቅት ከሰሜን ኤሴክስ ተመርጣ የፓርላማ አባል ስትሆን፣ ከዚህ በፊት የሴቶች እና እኩልነት ሚኒስትር፣ እንዲሁም የንግድ ጉዳዮች ፀኃፊ በመሆን አገልግላለች።
ባዴኖች ከናይጄርያዊ ቤተሰቦች በለንደን የተወለደች ብትሆንም፣ በናይጄርያ ሌጎስ ነው ያደገችው።16 ዓመት ሲሞላት በናይጄርያ በተባባሰው የፖለቲካ እና የምጣኔ ኃብት ቀውስ የተነሳ ወደ ዩኬ ተመልሳ በሕግ እና የኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ ተመርቃለች።
ከፖለቲካ ሕይወቷ በፊት 'ኮተስ' በተባለ የግል ባንክ ውስጥ ምክትል ዳይሬክተር እንዲሁም ለ 'ዘ ስፔክታተር' መጽሔት ዲጂታል ዳይሬክተር በመሆን አገልግላለች።
የቀድሞ እስረኛ የፖለቲካ አክቲቪስት
በዚህ ዓመት በነሐሴ ወር ላይ የተካሄደ ዓለም አቀፍ የእስረኞች ቅይይርን ተከትሎ ከተለቀቁ 26 እስረኞች መካከል አንዷ የሆነቸው የፖለቲካ አክቲቪስቷ ሊሊያ ቻኔሼቫ ነጻነቷን ካገኘች በኋላ ሩሲያን ለቅቃ ወጥታለች።
ቻኒሼቫ በሩስያ ባሽኮርቶስታን ግዛት ውስጥ የቀድሞውን ተቃዋሚ ፖለቲከኛ አሌክሲ ናቫልኒ ቢሮ ትመራ ነበር። ሥራዋ ሙስናን መመርመር እና ለፍትሃዊ ምርጫ እና የመናገር ነጻነት መሟገትን ያካትታል።
የተዋጣለት የፋይናንስ ባለሙያዋ ለናቫልኒ ከመስራቷ በፊት በሞስኮ ውስጥ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች በግብር አማካሪነት ሰርታለች።
እ.ኤ.አ. በ2021 በጽንፈኝነት ተከስሳ ተይዛ ዘጠኝ ዓመት ተኩል እስራት ተፈርዶባታል። ከመፈታቷ በፊት ሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር በእስር ቆይታለች።
የብዝሃነት እና አካቶ ዘመቻ አራማጅ
በኡጋንዳ የተመሳሳይ ጾታ ድርጊቶች በእስራት የሚያስቀጡ ወንጀሎች ናቸው። ካሻ ናባጌሴራ እነዚህን ጨቋኝ ሕጎች ለማስለወጥ ትታገላለች።
የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ሴት መሆኗን በግልጽ የተናገረች በመሆኗ በአፍሪካ በማኅበረሰቡ ላይ የሚደርሰውን መገለል በመከላከል ዘመቻ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ አሳርፋለች።
ናባጌሴራ፣ ጋዜጦች እና የኡጋንዳ መንግሥት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ላይ ያደረጓቸውን አሉታዊ ንግግሮች ተቃውማ ክስ በመመስረት ውጤታማ ክርክር አድርጋለች። በኡጋንዳ ፍርድ ቤቶች የተመሳሳይ ጾታ አፍቃርያንን የሚወነጅሉ ሕጎችን ተቃውማ ተከራክራለች፤ በአሁኑ ጊዜም በአውሮፓውያኑ 2023 የወጣውን ሕግ በመቃወም ላይ ነች።
ከንኩምባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ዲግሪ ያላት ሲሆን፣ ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፌሎሺፕ፣ እንደ ተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ፓርላማ እና የአፍሪካ ኮሚሽን ባሉ ከፍተኛ መድረኮች ላይ ደግሞ በብዝሃነት ላይ ለሚሰሯቸው ስራዎች አስተዋፅኦ አበርክታለች።
የሴቶች መብት ተሟጋች
ድምጿ እንዲሰማ በማሰብ ወደ ማኅበራዊ ሚድያ የሄደችው ፋውዝያ አል-ኦታዪቢ፣ በሳዑዲ አረቢያ ለረዥም ጊዜ የኖረውን የወንድ ጠባቂነት እንዲያበቃ ዘመቻ ከፍታለች።
ለጥያቄ በሚል በባለስልጣናት ከተጠራች በኋላ ግን አገሯን ለቅቃ ለመሄድ ተገድዳለች።
የሴቶች መብቶች ተሟጋች የሆነችው እህቷ በዚህ ዓመት፣ እንደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ድርጅቶች ገለጻ በምትለብሳቸው ልብሶች ምርጫ እና አመለካከቷን በኦንላየን ላይ በመግለጿ የተነሳ በቁጥጥር ስር ውላ የ11 ዓመት እስር ተፈርዶባታል።
አል-ኢታዪቢ እህቷ ከእስር እንድትለቀቅ ያለማቋረጥ ዘመቻዎችን ታካሄዳለች። በቅርቡ የሳዑዲ መንግሥት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሃሳባቸውን ያጋሩ ሰዎችን በማደን በቁጥጥር ስር አውሏል።
በጦርነት ወቅት የሚፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች ተሟጋች
ታዋቂዋ አክቲቪስት እና ደራሲ ሀላ አልካሪብ በአፍሪካ ቀንድ የሴቶች ስትራቴጂክ ኢኒሼቲቭ (SIHA) ዳይሬክተር ስትሆን፣ በሰፊው ክልል ውስጥ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን የሚያመላክቱ ስራዎችን ትመራለች።
በሱዳን ከሚያዝያ 2023 ጀምሮ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ፣ ሲሃ (SIHA) ከግጭት ጋር የተያያዙ ወሲባዊ ጥቃቶችን በመከታተል ለሴቶች እና ለሕጻናት ድጋፍ እያደረገች ነው።
እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2024 የወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ችግሩን “አስደንጋጭ” መጠን ያለው ሲል አስጠንቅቆ፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (RSF) “አሰቃቂ ወንጀሎች” ፈጽመዋል ሲል ከስሷቸዋል። አርኤስኤፍ ግን ውንጀላውን ውድቅ አድርጓል።
ሪፖርቱ ከግጭት ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች እስከ ሐምሌ 2024 ድረስ ቢያንስ 400 ሰዎች ድጋፍ እንዲያገኙ መላካቸውን ገምቷል። ይህንንም የችግሩ “ጫፍ” ብቻ መሆኑን ገልጿል።
የአካባቢ መሪ እና የደን ጥበቃ ተሟጋች
በቅርቡ በምዕራብ ቱርክ የኢኪዝኮይ አካባቢ መሪ ሆና የተመረጠችው አርሶ አደር ኔጃላ ኢሽክ ላለፉት አምስት ዓመታት የደን ጭፍጨፋን በመታገል ላይ ነች።
በአቅራቢያው የሚገኘው የአክቤለን ጫካ ለከሰል ማዕድን ማውጫ በተዘጋጀው ምክረ ሃሳብ ምክንያት ስጋት ውስጥ በወደቀበት ጊዜ፣ ኢሺክ እና ሌሎች የአካባቢው ሴቶች መሬቱን ለማዕድን ፕሮጀክቶች የሚመነጥረውን ለማስቆም ክስ በመመስረት እና የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ታግለዋል።
አንዳንድ ጊዜ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በፖሊሶች እና ደኑን ለመከላከል ዘብ በቆሙት ተቃዋሚዎች መካከል ከፍተኛ ግጭት ያስከተለ ቢሆንም፣ ኢሺክ እና ሌሎች የመንደሩ ነዋሪዎች ያለፍቃድ ወደ ጫካ መግባታቸው ቅጣትን ጨምሮ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች (በኋላ ተሰርዟል) እና ማስፈራሪያዎች ተቋቁመው መቆም ችለዋል።
ዓለምን የሚያስውቡት በአገር ውስጥ፣ በመስክ፣ በጎዳና ላይ፣ በትግል ውስጥ ያሉ ሴቶች... በመሆናቸው ያለጥርጥር ይከላከሉታል።
ኔጅላ ኢሲክ
የባሕል አክቲቪስት
በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ከሌሎች ጋር በመሆን የመሰረተችው የአብሮነት ባህል የተሰኘ ፕሮጀክት ቢሆንም፣ ዳንኤሌ ካንቶር እስካሁን ድረስ በቴላቪቭ ለሚገኙ ቤተሰቦች የምግብ እርዳታ ታቀርባለች።
አብራት ፕሮጀክቱን ከጀመረችው አልማ ቤክ ጋር በመሆን፣ ሰዎች ተገናኝተው የሚወያዩበት፣ የሚከራከሩበት፣ ባሕላዊ ከበራዎችን እና ወርክሾፖችን የሚያካሄዱበት አማራጭ ቦታ አላት።
በቅርቡ በእስራኤል እና በፍልስጤም ያሉ ባሕላዊ ምግቦችን የሚያሳይ መጽሐፍ አሳትማለች።
ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን በመካከለኛው ምሥራቅ በፍጥነት የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ዘላቂ የሆነ የሠላም ስምምነት እንዲደረስ ትጠይቃለች።
ሴቶች በተፈጥሮ ያገኙትን አዛኝነት ሲጠቀሙ፣ኢፍትሀዊነትን እና የፍትህ መጓደልን በታማኝነት በመለየት የወደፊት ሕይወታችንን ዳግም መቀየስ እንችላለን።
ዳንኤሌ ካንቶር
ሴናተር
ሱዛን ኮሊንስ በአሁኑ ወቅት ማይኔ ግዛትን በመወከል ለአምስተኛ ጊዜ እየሰራች ሲሆን፣ በአሜሪካ ሴኔት ውስጥ ረዥም ጊዜ ያገለገለች የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካይ ናት።
ብዙ ጊዜ ወሳኝ የሆኑ ሕጎችን ለማርቀቅ እና ለማጽደቅ ከተለያዩ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ትሰራለች። የሚድ ላይፍ ዉሜን አክት እና ቀድሞ ማረጥ ላይ የወጡ ሕጎችን ካስተዋወቁ ስድስት ሴናተሮች መካከል አንዷ ናት። በዚህ ሕግ መሰረት ማረጥ ላይ ለሚደረግ ምርምር፣ ሕክምና እና ግንዛቤ ማስጨበጫ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 275 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል።
ኮሊንስ ናሽናል አልዛይመርስ ፕሮጀክት አክትን ያረቀቀች ሲሆን፣አልዛይመርን ለመከላከል፣ ለማከም ብሔራዊ እቅድን ያስተባብራል። ተገቢው ግልጋሎት በበቂ ያልደረሳቸውን እና ዳውን ሲንድሮም ያለባቸውን ሰዎች ነግንዛቤ በማስገባት እስከ 2035 ድረስ ፕሮጀክቱ ፈንድ እንዲያገኝ ሰርታለች።
መምህር እና የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች
ሮዝሜሪ ዋይድለር-ዋልቲ በስዊዘርላንድ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ከሚማገቱ ሴቶች መካከል ቀዳሚ በመሆኗ እንዲሁም ከሌሎች ጋር በመሆን ማህበር በመመስረት የስዊዘርላንድ መንግሥት ጋር ለዘጠኝ ዓመት በአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት ተሟግታ ለመጀመሪያ ጊዜ በአየር ንብረት ጉዳይን ማሸነፍ ችላለች።
ዊድለር- ዋልቲ ከሌሎች 2,000 ሴቶች፣ የመዋዕለ ሕፃናት መምህር እና አማካሪዎች ጋር በመሆን የስዊዘርላንድ መንግሥት ከዓለም ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ ለሚመጣ የሙቀት ማዕበል የሚሰጠው ምላሽ የጤና መብታቸውን የሚጎዳ እንደሆነ እና በተለይ ደግሞ እድሜያቸው እና ጾታቸው ተጋላጭ እንዳደረጋቸው ተከራክራለች።
በሚያዝያ ወር ፍርድ ቤቱ መንግሥት በካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ የወሰደው እርምጃ በቂ አይደለም ሲል ውሳኔ አሳልፏል።
ምንም እንኳ የስዊዘርላንድ ፓርላማ ውሳኔውን ውድቅ ቢያደረገውም፣ጉዳዩ በአየር ንብረት ላይ ለሚነሱ ሙግቶች አዲስ ምሳሌ ሆኗል።
የሥነ ተዋልዶ መብት ተሟጋች
በ2022 ነሐሴ ወር አማንዳ ዙራውስኪ፣ከመውለጃ ጊዜዋ ቀድሞ የሽርት ውሃዋ ፈሰሰ።የሕክምና ባለሙያዎች ጽንሱ ሊተርፍ እንደማይችላ ነገሯት።
ዙራውስኪ በቴክሳስ የምትኖር በመሆኑ ጽንሱን ማቋረጥ ተከለከለች። በቴክሳስ የሰበር ሰሚ ችሎት የእናቲቱ ጤና አደጋ ላይ ካልሆነ በስተቀር ጽንስ ማቋረጥን አግዷል። ከሦስት ቀን በኋላ የደም ግፊቷ ከመደበኛው በታች ወርዶ ራሷን በመሳቷ እና የጤና ሁኔታዋ አደጋ ውስጥ በመውደቁ ጽንሱ እንዲቋረጥ ሆኗል።
በመጋቢት ወር 2023 ዙራውስኪ እና ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው 19 ሴቶች ግዛቲቱ ላይ ክስ መሰረቱ። ይህም በግዛቲቱ ጽንስ ማቋረጥ ከተከለከሉ በኋላ ክስ የመሰረቱ የመጀመርያዎቹ ሰዎች ያደርጋቸዋል። የቴክሳስ ሰበር ሰሚ ችሎት ጽንስ ማቋረጥ ላይ የጣለውን እገዳ ውድቅ አደረገው።
አሁን "በአገሪቱ የሥነ ተዋልዶ መብትን ለመመለስ እና ለመከላከል" ቃል ገብታ መታገል ቀጥላለች።
የታገቱ ሰዎች እንዲለቀቁ ተሟጋች
የ24 ዓመት ልጇ፣ ማታን፣ በሐማስ ጥቃት ወቅት የታገተባት ኢይናቭ ዛንጋውኬር፣ የልጇ እጮኛ ታግታ በእስረኛ ልውውጥ ወቅት ተለቅቃለች።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያለማቋረጥ ስለ ታገቱ ሰዎች፣ መሪዎች እርምጃ እንዲወስዱ፣ በየሳምንቱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን በማካሄድ ትወተውታለች።
ዛንጋውኬር ምንም እንኳ ከዚህ በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ገዢ ፓርቲ ድምጿን ብትሰጥም፣ የእስራኤል መንግሥት የታገቱ ሰዎችን ማስለቀቅ አልቻለም ብለው አጥብቀው ከሚተቹ መካከል ናት።
የቀሩት ታጋቾች እንዲለቀቅ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ትፈልጋለች።
ፖለቲከኛ
ሁአንግ ዢ፣ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ የፓርላማ መቀመጫ ስታሸንፍ ለፆታ እኩልነት በመታገል ትታወቃለች። ከዚህ በተጨማሪ በታይዋን የመጀመሪያዋ በግልጽ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ መሆኗን የተናገረች የሕዝብ እንደራሴ በመሆንም ታሪክ ሰርታለች።
በፖለቲካ ሕይወቷ ውስጥ ትልልቅ ማሻሻያዎችን አስተዋውቃለች። እነዚህም ላጤ ሴቶች እና ሴት ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ጥንዶች የወሊድ ሕክምና የማግኘት መብት እንዲከበር፣ መንግሥት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው እና ለአካል ጉዳተኛ ሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች ወጪን እንዲደጉም ማድረግ ይገኝባቸዋል።
በ2023 የጾታ ዝንባሌዋን ይፋ ካደረገች በኋላ ስለደረሰባት በደል በግልፅ ተናግራለች። በተቀነባበሩ የወሲብ ምስሎች ሰለባ በመሆኗም፣ በኢንተርኔት የሚካሄዱ ወሲባዊ ጥቃቶችን ለመዋጋት ያሉትን ሕጎች ለማጠናከር ትሰራለች።
እውነተኛ ጥንካሬ መሰረቱ ብዝኀነትን ማቀፍ ላይ ነው። በርካታ ሀሳብ ያላቸውን ባካተትን ቁጥር፣ በይበልጥ እንደ ሴቶች እና የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ያሉ ደካማ ተደርገው የሚታዩትን፣ ባቀፍን ቁጥር የበለጠ እየጠነከርን እንሄዳለን።
ሁአንግ ዢ
የሴቶች መብቶች ተሟጋች
በቻይና ለረዥም ጊዜ የሴቶች መብት ታጋይ የሆነችው ፌንግ ዩአን፣ ኢኳሊቲ ቤይዢንግ የተሰኘ ድርጅት መስራች እና ዳይሬክተር ነች። በ2014 ድርጅቱ የሕግ ማሻሻያዎች፣ የአቅም ግንባታ፣ እንዲሁም ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል የስልክ መስመር አስተዋውቋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የቻይናውን ሚ ቱ እንቅስቃሴ የጥቃት ሰለባዎችን የምትደግፍ ሲሆን፣ በሥራ ቦታ ጾታዊ ትንኮሳ እና ጥቃት እንዳይደርስ ለመከላከል ለሠራተኞች ስልጠና ትሰጣለች።
ፌንግ ከ1986 እስከ 2006 ድረስ በሴቶች ጉዳይ ላይ አተኩራ የምትሰራ ጋዜጠኛ ነበረች።
ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ፣ በሴቶች ዙርያ የሚሰሩ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሚድያዎች፣ ኤችአይቪ ኤድስ፣ አመራር፣ የወጣቶች አቅም ግንባታ ላይ ድጋፍ አድርጋለች። በቻይና እና ከዚያም ባሻገር የተለያዩ ሕትመቶችን አርትኦት በመስራት እና በማሳተም ተሳትፋለች።
የስደተኞች መብት ተሟጋች
በአሜሪካ ውስጥ በፖለቲካ እና በዘር ግንኙነት ላይ የምትሰራው ጉርሊን ኤም. ጆዜፍ፣ ለስደተኞች መብት ትወተውታለች።
በሴቶች የሚመራው እና የአፍሪካ ዝርያ ባላቸው ሰዎች ላይ የሚያተኩረው የሄይቲ ብሪጅ አሊያንስ መስራች ነች።
በእርሷ አመራር ሕብረቱ በዚህ ዓመት ዶናልድ ትራምፕ፣ የሄይቲ ስደተኞች 'የቤት አንስሳት ይበላሉ' ሲሉ በስፕሪንግ ፊልድ፣ ኦሃዮ በምርጫ ዘመቻ ወቅት ባደረጉት መሰረት የለሽ ንግግር ላይ የወንጀል ክስ መስርቷል።
ጆዜፍ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ስለሚደረጉ ሄይቲያውያን እርምጃውን በግንባር ቀደምትነት ትቃወማለች። ድርጅቷ በቅርቡ የባይደን አስተዳደርን፣ ከአገራቸው የቡድን ጥቃትን ሸሽተው ወደ አሜሪካ የመጡ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እንዲመለሱ ማድረግ እንዲቆም ጠይቋል።
የሴቶች መብቶች ተሟጋች
ኩርዳዊቷ ጋዜጠኛ እና አክቲቪስት ዚናሞዳሩስ ጎርጂ በ2019 ዚቫኖ የተሰኘ የሴቶች ማኅበር ከሌሎች ጋር በመሆን መሰረተች። ማኅበሩ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመቃወም ትምህርትን፣ ተቃውሞ ሰልፍን ይጠቀማል።
ማኅበሩን ከመሰረተች ጀምሮ ሁለት ጊዜ ያህል የታሰረች ሲሆን፣ መጀመርያ ላይ 'መንግሥትን የሚቃወም ፕሮፓጋንዳ በማካሄድ' ተከስሳ 21 ዓመት ተፈርዶባት ነበር። በአሁን ወቅት ወደ ሁለት ዓመት ከአራት ወር ተቀንሶላታል።
ሞዳሬስ ጎርጂ በኢራን የሕግ ማሻሻያ ለማምጣት ያለመው እና ሴቶችን የሚያገልሉ ሕጎች ላይ ትኩረቱን ያደረገው የአንድ ሚሊዮን ፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ አባል ናት።
ከዚህ በተጨማሪ የሴቶች ፖድካስት እና ስኬታማ የኩርድ ሴቶችን በሕጻናት መጽሐፍ መልክ ከሚያሳትሙት የሴት ኩርዳውያን ፎቶግራፍ ባለሙያዎች ቡድን ጀርባም አለችበት።
ከጾታዊ ጥቃት የተረፈች እና የመብት ተሟጋች
ጊሴል ማንነቷን ሳትደብቅ ታሪኳ ለዓለም እንዲደርስ በመፍቀድ የድፍረት እና የጽናት ምሳሌ ሆናለች።
የቀድሞ የትዳር አጋሯ አደንዛዥ ዕጽ ሰጥቶ ይደፍራት እንደነበር ያመነ ሲሆን፣ በርካታ ሌሎች ሰዎችም እንዲደፍሯት ይመለምል ነበር። በርካታ ደፋሪዎቿ ድርጊቱን ሲፈጽሙ ተቀርጸዋል።
በሕግ ማንነቷን አለመግለጽ ትችል የነበረ ቢሆንም፣ ሀፍረቱን ወደ አጥቂዎቹ ለመውሰድ በማሰብ፣ የፍርድ ስርዓቱ ግልጽ እንዲሆን፣ የተቀረፁት ቪድዮዎች አንዲታዩ ጠይቃለች። በድርጊቱ ላይ የተሳተፉት ከ50 በላይ ወንዶች ድርጊቱን መፈጸማቸውን ያመኑ ሲሆን፣አብዛኛዎቹ ወሲብ በመፈጸም ብቻ መሳተፋቸውን ጠቅሰው ተከራክረዋል።
የፍርድ ስርዓቱ ፍጻሜ ላይ ሲደርስ በመላው ዓለም የሚገኙ ሴቶች፣ ጉዳዩ የፈረንሳይን ሕግ፣ ደፈራ እና ፈቃድ መስጠት ላይ ያለውን አመለካከት፣ ይቀይረዋል በማለት በፈረንሳይቷ አያት ድርጊት የበለጠ ተነሳስተዋል።
የኮምፒውተር ሳይንቲስት
የሰው ሰራሽ አስተውሎትን (ኤአይ) በፍጥነት እየተቀበለ እና እየተገበረ በሚሄድ ዓለም ላይ፣ የኢንዱስትሪዎች የካርቦን አሻራ ቸል ይባላል።
የኤአይ ተመራማሪ ከሆኑት መካከል ግንባር ቀደም የሆነችው ሳሻ ሉቺያኖ፣ አልሚዎች የካርቦን ልቀት መጠናቸው ምን ያህል እንደሆነ እንዲለኩ የሚረዳ መሳርያ የፈጠረች ሲሆን ከ1.3 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አግኝቷል።
ሉቺያኖ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴል ላይ የሚሰራው እና ቴክኖሎጂውን ለበጎ ተጽዕኖ ለመጠቀም የሚንቀሳቀሰው 'ሀጊንግ ፌስ' ድርጅት የአየር ንብረትን ተወካይ ናት።
ትኩረቷ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘላቂነት ማሻሻል ላይ ነው፣ በተጨማሪም በዘርፉ ላይ የሚሰማሩ ጀማሪዎች የአየር ንብረትን ተፅእኗቸውን ለማነፃፀር ሊጠቀሙበት የሚችሉትን 'የኢነርጂ ምዘና ስርዓት' ለማዘጋጀት አቅዳለች።
የካንሰር ሕክምና ባለሙያ
ጆርጂና ሎንግ በታቀዱ ቴራፒዎች እና የሰውነትን የበሽታ መከላከል አቅም ተጠቅሞ በሚደረግ የካንሰር ሕክምና አማካኝነት የካንሰር ሞት የሌለበትን ዓለም ማየት ትፈልጋለች።
ሎንግ የሜላኖማ ኢንስቲትዩት አውስትራሊያ ዋና ዳይሬክተር ስትሆን፣ ባልደረባዋ እና ጓደኛዋ ሪቻርድ ስኮሊየር በአደገኛ የጭንቅላት ካንሰር ከተያዘ በኋላ፣ ከሌሎች ጋር በመሆን በዓለም ላይ የመጀመርያ የሆነውን ሕክምና በመንደፍ ከሕመሙ ነጻ እንዲሆን በማድረጓ በ 2024 ታዋቂ ለመሆን በቅታለች።
ሎንግ እና ቡድኗ እንዲሁም ሕመምተኛውን ጨምሮ ዕጢውን ለማስወገድ ቀዶ ጥገና ከመደረጉ በፊት ጥምር መድኃኒት ጥቅም ላይ ሲውል፣ የበሽታ መከላከያ አቅምን ተጠቅሞ የሚደረግ ሕክምና በተሻለ ሁኔታ እንደሚሰራ ደርሰውበታል።
በሜላኖማ ላይ ለበርካታ ዓመታት ባደረጉት ምርምር እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ውጤት የተገኘ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የቆዳ ካንሰር ሕሙማንን ሕይወት ማዳን ተችሏል።
የቀጣዮ ትውልድ መሪዎች ርህራሄ እና ሰብዓዊነትን ማበረታታት አለባቸው፤ ሰዎች ያረጁ እና ያፈጁ ስርዓቶችን እንዲገዳደሩ እንዲሁም ለችግሮች ፈጠራ የታከለባቸው መፍትሄዎችን እንዲከተሉ ማበረታታት ይጠበቅባቸዋል።
ጆርጂና ሎንግ
የይዘት ተቆጣጣሪዎች ማኅበር መሪ
ካውና ማልጉዊ በቴክኖሎጂ እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንዱስትሪ ውስጥ ለሚሰሩ ሠራተኞች መብቶች ትሟገታለች። በሙያዋ ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት ስትሆን በናይጄርያ የይዘት ቁጥጥር ባለሙያዎች ማኅበርን ትመራለች። በተጨማሪም የሰው ሠራሽ አስተውሎትን በማሰልጠን፣ የማይታይ ሠራተኛ በመፍጠር ሂደት ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ትሰራለች።
ከዚህ ቀደም ለፌስቡክ የይዘት ተቆጣጣሪ ሆና ሰርታ የምታውቅ ሲሆን፣ በዚህም ወቅት የሚደፈሩ ሰዎችን፣ ራሳቸውን የሚያጠፉ እና ሕጻናት ላይ ጥቃት ሲፈጸም የሚያሳዩ ቪድዮዎችን ለማየት ትገደድ ስለነበር እንቅልፍ ለማጣት እና ለመረበሽ እንደተጋለጠች ትናገራለች።
በኬንያ ለሜታ የሰው ኃይል ቀጥሮ ሲያሰራ የነበረው ኩባንያ ውስጥ ያለውን ዝቅተኛ የሥራ ሁኔታ መጋለጡን ተከትሎ፣ ከሕግ ውጪ ከሥራ በመባረራቸው የፌስቡክ እናት ድርጅትን፣ ሜታን፣ ፍርድ ቤት ከከሰሱ 184 ሰዎች መካከል አንዷ ናት።
በአውሮፓ ፓርላማም ቀርባ ስለይዘት ተቆጣጣሪዎች መብት የተናገረች ሲሆን ስለነበረው ሁኔታም ምስክርነቷን ሰጥታለች።
ሴቶች ይህንን የተበላሸ ዓለም ስለ አእምሮ ጤና እና የቴክኖሎጂ መሻሻሎች አጠቃላይ ምልከታ በማምጣት መገዳደር እና መቀየር እንችላለን።
ካውና ማልጉዊ
የሱፐርሂውመንስ ማዕከል መስራች
ሩስያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ፣ ኦልጋ ሩድኔቭ በግጭቱ የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት የሆነ ነገር ማድረግ እንዳለባት ተሰማት።
በጦርነቱ የአካል ክፍሎቻቸውን ያጡ ሰዎች በበርካቶች እንደ ተጎጂ ነው የሚታዩት፣ ነገር ግን ሩድኔቭ መስጠት የምትችለው ድጋፍ ሁሉ የሚገባቸው 'ልዕለ ሰብዕና ያላቸው ናቸው' ትላለች።
በሌቪቭ እርሷ በበላይነት የምትመራው እና በባለሙያዎች የሚታገዝ የሱፐርሂውመንስ ትራውማ ማዕከል አቋቋመች። ማዕከሉ የተለያዩ የአካል ድጋፎችን ለሕሙማን የሚያመርት ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ የማገገምያ ማዕከልም ተከፍቷል።
ሥራ በጀመሩ በሁለት ዓመት ውስጥ ብቻ ከ 1000 ሰዎች በላይ የአገልግሎታቸው ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
ጥንካሬ ማለት ዘወትር ማለዳ እየነቁ የአደጋ ደውሎችን መደወል እና ለአገር መዋጋት ነው። የራስን 'ለምን እኔ ላይ?' ሳይሆን "ለምንን? ዳግም መፈለግ ነው። በየዕለቱ ትንሽ እያለኝ በርካታ ነገሮችን መከወን ነው።
ኦልጋ ሩድኔቫ
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ባለሙያ
ስኔሃ ሬቫኑር ገና በ20 ዓመቷ ከሁኔታዎች ቀድማለች። በ30 አገራት ከ1,300 በላይ አባላት ያሉት ደኅንነቱ ለተጠበቀ፣ ፍትሃዊ ሰው ሠራሽ አስተውሎት(AI) የሚሠራ ኢንኮድ ጀስቲስ የተሰኘ ዓለም አቀፍ የወጣቶች እንቅስቃሴ መሥርታለች።
ሬቫኑር በቴክኖሎጂ የሚመጡ ስጋቶችን ለመቀነስ እና ወጣቶችን ወሳኝ በሆኑ ንግግሮች ውስጥ ለማካተት ትሠራለች።
በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ስትሆን፣ በኤአይ እና ዲጂታል ፖሊሲ ማዕከል ደግሞ በክረምት ትሳተፋለች።
በቅርቡ በታይም መጽሔት በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ተደማጭነት ካላቸው 100 ግለሰቦች መካከል አንዷ ተብላ ተጠቅሳለች።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት አስደማሚ እምቅ አቅም ከመጨመሩ በፊት ከአደጋዎቹ ለመቅደም እድሉ አለን። ለእኔ ይህ የመቋቋም ብቃት ነው፤ ካለፈው በላይ መነሳት የወደፊቱን ዳግም ለማሰብ ካለፈው ልቆ መገኘት።
ስኔሃ ሬቫኑር
የስነ ልቡና አማካሪ
የስነልቡና ባለሙያዋ ሳሚያ፣ ቢቢሲ ደህንነቷን ለመጠበቅ ሲል እውነተኛ ስሟን አይጠቀምም፤በሶርያ ለዓመታት የዘለቀውን ግጭት ተከትሎ የአእምሮ ቁስለት ላጋጠማቸው ሰዎች ድጋፍ ታደርጋለች።
ለረዥም ዓመታት የዘለቀው ጦርነት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ በሕይወት የተረፉት ደግሞ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ የአእምሮ ጤና ቀውስ ውስጥ፣ ለድብርት እና ድብታ ተጋልጠው ሕይወታቸውን እየገፉ ይገኛሉ።
በኢንተርናሽናል ሬስኪዩ ኮሚቲ በሚደገፍ ክሊኒክ ውስጥ የምትሰራው ሳሚያ፣ ተፈናቀለው በሰሜን ምሥራቅ ሶርያ መጠለያ ጣብያ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸው የምክክር አገልግሎት ትሰጣለች።
የበጀት እጥረት ቢኖርም፣ የሕሙማኖቿን የአእምሮ ጤና ለማሻሻል እና በቀውስ ውስጥ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ትሰራለች።
የሥነ ሕይወት ባለሙያ
ፈር ቀዳጅ ሳይንቲስቷ ሲልቫና ሳንቶስ በጄኔቲክሰ ላይ ያደረገችውን ወሳኝ ግኝት፣ በምትኖርበት አካባቢ የሚኖር ቤተሰብ በማይታወቅ በሽታ ተጠቅቶ በማግኘቷ የተነሳ፣ ሙሉ በሙሉ ለእድል አሳልፋ ትሰጣለች።
ከዚያም ይህ በሰሜን ምስራቅ ብራዚል ያልተለመደ እና የነርቭ ስርዓትን ቀስ በቀስ የሚጎዳውን በሽታ ስፖአን (SPOAN) ሲንድሮም መሆኑን በመለየት ቀስ በቀስ የአካል አለመታዘዝን እንደሚያስከትል ደረሰችበት።
ከ20 ዓመት በፊት ሰሪና ዶስ ፒንቶስ በምትባል ከተማ ምርምሯን ከጀመረች ጀምሮ፣ በሕመሙ የተጠቁ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ሕክምና እኝዲያገኙ አድርጋለች።
በምርምሯም ይህ ያልተለመደ የጄኔቲክ በሽታ እና በድህነት በተጠቁ የብራዚል ገጠራማ አካባቢዎች የቅርብ ዝምድና ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸም ጋብቻ ያለውን ግንኙነት አጥንታለች።
የመቋቋምን ብቃት እንዴት ነው የምናሳየው? ሕይወት ዑደት መሆኗን በመረዳት። በድርቅ ወቅት እንተርፋለን፤ በዝናባማ ወቅት ደግሞ እናብባለን፤ እናፈራለን።
ሲልቫና ሳንቶስ
ነርስ እና የትምህርት ቤት መሥራች
ነርስ ሪክታ አክተር ባኑ በምትኖርበት ራቅ ባለው ሰሜናዊ ባንግላዴሽ፣ ኦቲስቲክ ወይም የአካል ጉዳተኛ ልጅ መውለድ እንደ እርግማን ይታያል።
ሴት ልጇ ኦቲዝም እና ሴሬብራል ፓልሲ ያለባት ሲሆን፣ በአካባቢያቸው የሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዳትገባ ስትደረግ፣ መሬቷን ሸጣ የራሷን ትምህርት ቤት ገነባች።
የሪኪታ አክተር ባኑ የመማር ውስንነት ያለባቸው ትምህርት ቤት አሁን 300 ተማሪዎችን የመዘገበ ሲሆን፣ በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ በማኅበረሰቡ እይታ ላይ በጎ ተጽዕኖ አምጥቷል።
ትምህርት ቤቱ በመጀመሪያ የተገነባው ኦቲዝም ወይም የመማር ውስንነት ላለባቸው ልጆች ቢሆንም፣ አሁን የተለያዩ የአእምሮ እና የአካል እክል ያለባቸውን ተማሪዎችን ይቀበላል።
የብዝኀ ሕይወት ባለሙያ
የሥነ ሕይወት ባለሙያ ብሪጊት ባፕቲስት ጾታዋን የቀየረች ሲሆን፣ በብዝኀ ሕይወት እና በጾታ ማንነት መካከል ያለውን የጋራ መስመር ታጠናለች።
የብዝኃ ሕይወትን የበለጠ ለመከላከል መልክዓ ምድርን እንዲሁም የተለያዩ ዝርያዎችን ስታጠና የጾታ ዝንባሌ አተያይዋን ትጠቀማለች። በ2018 በቴድቶክ ላይ ባደረገችው ንግግር፣ በኮሎምቢያ የሚገኘው ኪውንዲዮ ዋክስ ፓልም የተባለው ዛፍ በሕይወት ዘመኑ "ከወንድ እንዴት ወደ ሴት ጾታ እንደሚቀየር ሳይንስ የሚያብራራበትን" መንገድ በመጥቀስ አተያይዋን አብራርታለች።
ታዋቂዋ ምሑር ባፕቲስት ለ10 ዓመት ያህል የአሌክሳንደር ቮን ሁምቦልድት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የነበረች ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ዘላቂነት ያለው ሥራ ፈጠራ ላይ አተኩሮ የሚሰራው እና ቦጎታ የሚገኘው ዩኒቨርሲዳድ ኢኤን ፕሬዝዳንት ናት።
በርከት ያሉ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃርያን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲመጡ የተሻለ የገንዘብ ድጋፍ እንዲኖር ዘመቻ ታካሄዳለች።
የዲአይዋይ ሳይንስ ኪትስ ዲዛይነር
ሱዳን ተወልዳ ለንደን ያደገችው ኤርትራዊት ሳራ ቤርካኢ፣ዩኒቨርስቲ ለመግባት ከቤተሰቧ የመጀመርያዋ ነች።
የአምበሳ ፕሌይ መስራች ስትሆን፣ ለሕጻናት መጫወቻዎች የሚያመርተው፣ እንዲሁም መጫወቻዎችን ዲዛይን እንዲያደርጉ የሚያበረታታው ዲአይዋይ ዲዛይንስ መስራች ናት።
የቤርካኢ ሥራ በተለያዩ አገራት ከትምህርት ውጪ የሆኑ ሕጻናት፣ ትምህርትን በጨዋታ ውስጥ እንዲያገኙ ማስቻል ነው።ይህ ጽንሰ ሀሳብ የመጣላት ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ ለተፈናቀሉ ሕጻናት በ2019 ስቴም (STEM) ስታስተምር ነው።
የፈጠራ ሀሳቦቿ በፎርብስ 30፣ ከ30 በታች ማህበራዊ ተፅእኖ ፈጣሪዎች በሚል እውቅና አግኝተዋል።
ጥንካሬ በተግባር ብሩህ ተስፋ ማድረግ፣ የጸና ቁርጠኝነት፣ በፍቅር ላይ ተመስርቶ፣ ለተሻለ ወደፊት መስራት ነው።
ሳራ ቤርካኢ
የአየር ንብረት ፍትህ ተሟጋች
ናይጄራዊቷ የአካባቢ ጥበቃ እና የሴቶች መብት ተሟጋች አዴኒኬ ቲቲሎፔ ኦላዶሱ፣ 'አይ ሊድ ክላይሜት አክሽን'፣ የተሰኘ ድርጅት መስርታ ሴቶች እና ወጣቶች ስለ አየር ንብረት ለውጥ እንዲታገሉ እያደረገች ነው።
ናይጄርያ፣ ኒጀር፣ ቻድ እና ካሜሮንን የሚያዋስነው የቻድ ሐይቅ ላይ በደረሰው አካባቢያዊ ተጽዕኖ፣ የውሃ መጠኑ በመቀነሱ የተነሳ ግጭቶችን በማባባሱ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ሠርታለች።
የኦላዶሱ ሥራ አካባቢያዊ እና ማሕበራዊ ጉዳዮችን ይነካል። በይበልጥ ደግሞ እነዚህ ጉዳዮች የአፍሪካን ሴቶች የሚመለከቱ በመሆናቸው፣ በረሃማነት በሚያጠቃቸው እና የምግብ ዋስትና አደጋ ላይ በወደቀባቸው ስፍራዎች ዘላቂነት ያለው አስተራረስ ክህሎትን ታስተምራለች።
ከ2019 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች ላይ የምትሳተፍ ሲሆን፣ ፖሊሲ አውጪዎች በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም ቀዳሚ አጀንዳቸው እንዲያደርጉ ትወተውታለች።
የአየር ንብረት ለውጥ ከማሸነፍ ውጪ ሌላ ምርጫ ያልተወልን የመገዳደር ጉዳይ ነው።ከዚህ ቀውስ ለመትረፍ፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ላይ ሀብታችንን ማፍሰስ አለብን።
አዴኒኬ ቲቲሎፔ ኦላዶሱ
አርሶ አደር እና አሰልጣኝ
በግብርና ትምህርት ቤት ውስጥ የምትሰራው ናኦሚ ቻንዳ፣ ማኅበረሰቧ የሚጠቀምበትን መሬት አክብሮ መንከባከብ የሚችልባቸውን ዘዴዎችን የማስተማር ተልዕኮ ሰንቃለች።
ትኩረቷ የአየር ንብረትን ከግንዛቤ ያስገቡ ክህሎቶች፣ ዝቅተኛ ውሃ የሚጠቀም የጠብታ መስኖ፣ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎች፣ ላይ ሲሆን ሴቶችም የአየር ጠባይ ለውጥ መከላከል ማዕከል ናቸው።
ቻንዳ በሴቶች ላይ ከሚሰራው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባገኘችው ድጋፍ፣ በዛምቢያ ሰሜን ምስራቅ የሚገኙ 150 ወጣት ሴቶችን በአስተራረስ ቴክኒኮች፣ አደገኛ የሆኑ የወቅቶች መለዋወጥ አነስተኛ መሬት ባላቸው ገበሬዎች ላይ ያለውን የከፋ ተጽዕኖ፣ እና የአየር ጠባይ ለውጥን መቋቋም ላይ አሰልጥናለች።
የማሕጸን እና ጽንስ ሐኪም
ባለፈው ዓመት በሱዳን በምትሰራበት ጤና ተቋም አቅራብያ ከባድ ውግያ በተቀሰቀሰበት ወቅት ዶ/ር ሳፋ አሊ ሞሐመድ ዩሲፍ፣ ከባልደረቦቿ ጋር ሆስፒታሉን ትታ ለመውጣት ፍቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች።
የጽንስና ማህፀን ሕክምና አማካሪ የሆነችው ዶ/ር፣ በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ግጭት በተቀሰቀሰበት ወቅት በጎ ፍቃደኛ ሰራተኞች እና ነፍሰ ጡር እናቶችን ደህንነቱ ወደተጠበቀ ቦታ እንዲዛወሩ አድርጋለች።
በአሁኑ ወቅት በአል-ሳዑዲ የእናቶች ሆስፒታል፣ የማሕጸን እና ጽንስ ሕክምና ባለሙያዎች በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት ለሴቶች እና የሚወልዱ እናቶች ቀዶ ሕክምና የሚያካሄዱት እና የሕክምና ድጋፍ የሚሰጡት በከፍተኛ ችግር ውስጥ ሆነው ነው።
ከዚህ በተጨማሪ 20 አዲስ ተመራቂ ሴት ዶክተሮችን፣ የሚያጋጥሙ የባለሙያዎችን እጥረት ለመቅረፍ፣ በማሕፀን እና ጽንስ ሕክምና ታሰለጥናለች።
በሴቶች ትግል ውስጥ ፈውስ፣ ፍትህ እና ወደፊት ያለፍርሀት የምንኖርበት ተስፋ አለ ብዬ አምናለሁ። ነገሮች በከፉበት ጊዜ እንኳ ተስፋ እንዳለ የሚያስታውሰኝ የእነርሱ ጥንካሬ ነው።
ሳፋ አሊ
የግብርና መሀንዲስ
በጦርነቱ የተነሳ በጋዛ የውሃ እጥረት ሲከሰት፣ኤናስ አል-ጋሁል መፍትሄ መፈለግ እንዳለባት ተሰማት።
የግብርና መሀንዲሷ እንደ እንጨት፣ ጠርሙስ፣ ላስቲክ የመሳሰሉ ዳግም ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሶችን በመጠቀም በፀሐይ ብርሃን የሚሰራ የባሕር ውሃን አጣርቶ ለመጠጥ ውሃነት የሚያውል መሳርያ ሰርታለች።
መሳርያው በደቡብ ጋዛ ሰርጥ በካህን ዩኒስ አካባቢ በድንኳን ውስጥ ለሚኖሩ ተፈናቃዮች፣ ከጥቅምት 2023 ጀምሮ በጋዛ የውሃ እና ንጽህና ተቋማት በመጎዳታቸው አልያም በመውደማቸው፣ ሕይወት አድን ሆኖላቸዋል።
ከመኖርያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን ለመርዳት ያላትን ክህሎት ለመጠቀም ቁርጠኛ የሆነችው አል-ጋሁል፣ በፀሐይ ብርሀን የሚሰራ ማብሰያ ሰርታለች፤ ምንጣፍ እና ቦርሳዎችን ዳግም ጥቅም ላይ ከሚውሉ ቁሶች መሥራትን ራሷን አስተምራለች።
የሕጻናት ሕክምና ባለሙያ
ሺሬን አቤድ በየዕለቱ የሚደርሱ የቦምብ ጥቃቶች እና የቁሳቁስ እና መድሃኒት እጥረቶች በጋዛ ለሕጻናት የምታደርገውን እንክብካቤ አላስቆማትም።
በ2023 እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረች ወዲህ የምትኖርበት ቤት በመውደሙ የተነሳ ተፈናቅላለች። ነገር ግን እንደ ጨቅላ ሕጻናት ስፔሻሊስትነቷ በተፈናቃዮች መጠለያ ጣብያ የሚገኙ ሕጻናትን መንከባከቧን ቀጥላለች።
በጋዛ ዋናው ሆስፒታል የጨቅላ ሕጻናት ክፍልን ውስጥ የነበራትን የአንድ ዓመት ቆይታ እንዲሁም በቅርቡ በአል-ሺፋ ሆስፒታል የእናቶች ማዕከል ዳይሬክተር ልምድ በመቀመር፣የሕክምና ባለሙያዎች በውስን ሀብት ሕይወት አድን የሆነ ሕክምና መስጠት የሚችሉበትን የድንገተኛ ሕክምና ፕሮቶኮል በማዘጋጀት ዶክተሮችን አሰልጥናለች።
ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ሁኔታዎች ሁለት ልጆቿን ይዛ ከጋዛ እንድትወጣ አስገድዷታል። ነገር ግን አቤድ፣ በርቀት ሆና በጋዛ ያሉ ዶክተሮችን ታግዛለች።
የዘላቂነት ሥራ ፈጣሪ
ሺልሺላ አቻርያ በኔፓል ትልቁን ፕላስቲክን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ስራን ትመራለች። አቭኒ ቬንቸርስ ስትል የሰየመችው የቆሻሻ አወጋገድ አስተዳደር ከተገለሉ ማኅበሰረቦች የመጡ ሰዎችን ቀጥሮ የሚያሰራ ሲሆን በርካታ ሴቶችም በአረንጓዴ ዘርፍ ላይ እንዲሳተፉ ትኩረት አድርጎ ይሰራል።
አቻርያ በ2014 'ኖ ታንክስ፣ አይ ካሪ ማይ ኦውን ባግ' የተሰኘ ዘመቻን በግንባር ቀደምትነት የመራች ሲሆን፣ ከፕላስቲክ የተሰሩ የመገበያያ ቦርሳዎችንም እንዲታገዱ አድርጓል።
የአየር ንብረት እና የአወጋገድ አስተማሪዋ አቻርያ ተራራ ወጪዎች የጣልዋቸው ቆሻሻዎችን የሚያጸዳው ትልቁ ዓመታዊ ሂማሊያስን የማጽዳት ዘመቻ ጀርባም አለችበት።ከ2019 ጀምሮም 119 ቶኖችን መሰብሰብ ችሏል።
በሥራዎቿ፣ የተወሰኑት እነዚህ ቆሻሻዎች የአገሬው ሴቶች እንደ ዘንቢል፣ ምንጣፍ፣ እና ጌጣጌጦችን አምርተው በመሸጥ ኑሯቸውን እንዲደግፉበት ታደርጋለች።
የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪ
የወሲብ ጤና አስተማሪዋ ኑር ኢማም፣በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ አካባቢዎች እንደ ነውር የሚቆጠሩት የወር አበባ ንጽህና፣ የሥነ ተዋልዶ ጤና፥ እንዲሁም ስለ ወሲብ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ታተኩራለች።
ኢማም 'ማዘርቢንግ' የተሰኘ ተቋምን ከመሰረቱት መካከል አንዷ ስትሆን ዋና ሥራ አስኪያጅም ናት። ኩባንያው የሴቶች የጤና አገልግሎትን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል።ይህንንም ለማገዝ በካይሮ ክሊኒክ ከፍተዋል።
በመረጃ ላይ በተመሰረተ እውቀት ሴቶች ስለ አካላቸው እንዲያውቁ ማድረግ ያለመች ሲሆን፣ በእርግዝና መከላከያ ላይ ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን ያለ ፍርሀት እና መሸማቀቅ እንዲረዱ ትሰራለች።
ኬሚካል ባዮሎጂስት
አያቷ በነበራቸው የባህል መድኃኒት እውቀት ትመሰጥ የነበረው ሳይንቲስቷ ሮዛ ቫስኩዝ ኢስፒኖዛ፣ በፔሩ አማዞን ውስጥ ያለውን ብዝሃ ሕይወት ለመጠበቅ እጅግ የላቀ ሳይንስ እና ባሕላዊ እውቀትን በማጣመር በመሥራት ላይ ትገኛለች።
የአማዞን ሪሰርች ኢንተርናሽናል መሥራች በመሆኗ የጫካውን ያልተነካ የብዝሃ ሕይወት ለመመርመር ከአገሬው ቀደምት ማኅበረሰቦች ጋር በጥምረት ትሠራለች።
የኢስፒኖዛ ሥራ ብዙ ጊዜ በምድራችን ላይ ሩቅ ወደ ሆኑ ሥነ-ምህዳሮች በመጓዝ፣ በአማዞን ታዋቂ የሆነው ፍል ወንዝ (ቦይሊንግ ሪቨር) ውስጥ አዳዲስ ባክቴሪያዎችን ፈልጎ ማግኘትን እና በፔሩ ውስጥ የማይናደፉ ንቦች እና ለመድኃኒትነት የሚያገለግል ማር ላይ የመጀመሪያውን ኬሚካላዊ ትንተና መሥራትን ያጠቃልላል።
በተጨማሪም በደቡብ አሜሪካ ከሚገኙት ትላልቅ ነባር ሕዝቦች መካከል አንዱ የሆነው የአሻንካ ሕዝብ ዓለም አቀፍ አምባሳደር ነች።
አርሶ አደር
ኦልጋ ኦሌፊሬንኮ አባቷ በ2015 ሲሞት፣ ሕልሙን ለማሳካት በሚል ወደ ግብርና ሥራ ገባች።ለእርባታ የሚሆኑ እንስሳትን ከገዛች በኋላ፣ወደ ሥራ ብትገባም የገንዘብ እጥረት ስለገጠማት ከብቶቹን ሸጠቻቸው።
ነገር ግን በዶንባስ የባህር ኃይል ልዩ ኃይል አዛዥ ሆኖ በጦር ሜዳ የተገደለው አባቷን ሕልም ወደ ጎን ማለት አልፈለገችም።
ባለፈው ዓመት ከዩክሬን የቀድሞ ሠራዊት ፈንድ ልታገኝ የምትችልበትን የንግድ ዕቅድ ከሰራች በኋላ ውጤታማ ሆናለች።
ኦሌፊሬንኮ ዘመናዊነት ላይ ትኩረቷን አድርጋ ወደ ግብርና ሥራዋ ዳግም ተመልሳለች። በዚህም የተነሳ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የምትጠቀም ሲሆን፣ በአመራሯ እና በሥራዋ እንደ ምሳሌ ለሚያያት የአካባቢው ማኅበረሰብም የሥራ እድል ፈጥራለች።
ባዩኬሚስት እና የኖቤል ሎሬት
የሃንጋሪ ተወላጇ ባዮኬሚስት ካታሊን ካሪኮ ያደረገችው ወሳኝ ምርምር በባዮኤንቴክ/ፋይዘር እና ሞደርና የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለመፍጠር ጥቅም ላይ ውለዋል።
ይህም የምርመር ስራዋ “በዘመናችን በሰው ልጅ ጤና ላይ ከፍተኛ ስጋት በተደቀነበት ወቅት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት ክትባት በማምረት” የኖቤል ሽልማት(ከባልደረባዋ ድሩ ዌይስማን ጋር) እንድታገኝ አድርጓታል።
ኤምአርኤን( mRNA) ዲኤንኤአችንን ወደ ፕሮቲኖች የሚተረጉመው፣ እጅግ በጣም ተሰባሪ እና ለመስራት አስቸጋሪ ነው። ካሪኮ ግን በመድሀኒት ቅመማ ውስጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት እርግጠኛ ነበረች።
ቴክኖሎጂው ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት በሙከራ ደረጃ ላይ ነበር። አሁን ግን በዓለም ዙሪያ ለሚኖሩ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ከጽኑ የኮቪድ-19 ሕመም ለመከላከል ተሰጥቷቸዋል።
ምንጊዜም ሌሎች መስራት ባለባቸው ላይ ሳይሆን አንቺ መስራት በምትችይው ነገር ላይ በማተኮር ለግብሽ ሥሪ። ከወደቅሽ ከዚያ ተማሪ። ተነስተሽ በተመሳሳይ ትጋት ቀጥይ።
ካታሎን ካሪኮ
ፕሮግራመር እና የዳታ ሳይንቲስት
የአፍ መፍቻ ቋንቋዋ የሆነው ናሁአትል፣ ገብሬላ ሳላስ ካብሬራ እስክትሳተፍበት ድረስ፣ በጉግል የመተርጎሚያ ድረ ገጽ ላይ አልነበረም።
ኢንጂነሮቹ ከግዙፉ የቴክ ኩባንያ የሥነ ልሳን ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የሜክሲኮ የነባር ማኅበረሰብ ቋንቋዎች ወደ ጎግል መተርጎምያ እንዲገቡ አድርገዋል።የናሁኢትል መተርጎሚያም ከባለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ለሕዝብ ግልጋሎት ክፍት ሆኗል።
የሳላስ ሥራ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን አቅም ተገቢው ውክልና የሌላቸውን ቋንቋዎች ለሟጉላት፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከነባር ማኅበረሰብ የተገኙ ሴቶችን ተሳትፎ ለማጉላት ተጠቅሟል።
በስፔን ማድሪድ በሚገኘው ዩኒቨርሲዳድ ፖሊቴስኒሲያ ዳታ ሳይንስ ያጠናች ሲሆን፣በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ኦብጀክት ኦሬይንትድ ፕሮግራሚንግ ስፔሻላይዝ አድርጋለች።
የሴቶች ጥንካሬ ነበልባሉ የማይበርድ፣ሕመምን ወደ ዓላማ የሚቀይር እንዲሁም ለሚከተሉት ደግሞ መንገድን የሚያበራ ነው።
ገብሬላ ሳላስ ካብሬራ
ጠፈርተኛ
ሰኔ 5 ዕለት የናሳ ጠፈርተኛዋ ሱኒታ ዊሊያምስ ቦይንግ ስታርላይነር የጠፈር መንኮራኩርን ስትሳፈር በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ለስምንት ቀን ለመቆየት በሚል ነበር።
ነገር ግን በመንኮራኩሩ ላይ በተከሰቱት የቴክኒክ ችግር የተነሳ ዊሊያምስ እና የሥራ ባልደረባዋ ባሪ ዊልሞር እስከ የካቲት 2025 ወደ ምድር እንደማይመለሱ ተነግሯቸዋል።
ዊሊያምስ፣ ጡረታ የወጣች የባሕር ኃይል ሄሊኮፕተር አብራሪ እና ስፔስ ላይ ብዙ ጉዞዎችን በማድረግ በሴቶች ክብረወሰን ያስመዘገበች፣ በ2007 ደግሞ ህዋ ላይ ማራቶን በመሮጥ የመጀመሪያው ሰው ናት።
ምንም እንኳን አሁን ከምድር በላይ 400 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከጓደኞቿ እና ከቤተሰቧ ርቃ ብትገኝም፣ የተራዘመውን ቆይታዋን በጽናት እና በጥሩ ስሜት ተቀብላ የጠፈር መንኮራኩሯን “ደስተኛ ቦታዬ” በማለት ገልጻለች።
የስቴር ክራሸር ክለብ መስራች
የዊልቸር ተጠቃሚ የሆነችው ሱቢን ፓርክ በሴኡል መሄድ የምትፈልጋቸው ብዙ ቦታዎች ተደራሽ ባለመሆናቸው የተነሳ፣ ከዚህ ቀደም የአይቲ ሥራ አስኪያጅ መሆኗን ተጠቅማ ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ መስራት ጀመረች።
ፓርክ ለትርፍ ያልተቋቋመው እና በደቡብ ኮርያ ለዊልቸር ምቹ ያልሆኑ ቦታዎችን እና መስመሮችን መረጃ የሚሰበስበው የስቴር ክራሸር ክለብ አጋር መስራች ናት።
ይህ ፕሮጀክት ለተጠቃሚዎች ተደራሽነትን የሚያሳይ ካርታ መፍጠር ዓላማው አድርጎ ይሰራል።
እስካሁን ድረስ ከ2,000 በላይ ዜጎች በስታየር ክሬሸር ክለብ የመረጃ ቋት ላይ አስተዋፅዖ ያደረጉ ሲሆን በመላ ሀገሪቱ 14,000 አካባቢዎች ተደራሽነታቸው ተፈትሿል።
የቢቢሲ100 ሴቶች በመላው ዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ እና አርዓያ የሆኑ ሴቶችን በየዓመቱ የሚያቀርብ ነው። ሴቶችን በዋናነት የሚያጎሉ እና በቢቢሲ ሁሉም ማሰራጫዎች የሚተላለፉ እና የሚታተሙ ዘጋቢ ፊልሞችን፣ ፊቸሮችን፣ ዜናዎችን እና ቃለምልልሶችን እንሰራለን።
የቢቢሲ 100 ሴቶችን በኢንስታግራም እና ፌስቡክ ይከታተሉ። #BBC100Women ላይ የሚካሄዱ ውይይቶችን ይከታተሉ።
የቢቢሲ 100 ሴቶች ቡድን አባላት በጥናት፣ ከ41ዱ ቋንቋዎች አገልግሎት፣ እንዲሁም ከቢቢሲ ሚድያ አክሽን ስም ዝርዝሮችን ይሰበስባል።
ባለፉት 12 ወራት የዜና ርዕስ የሆኑ ወይንም ወሳኝ ታሪክ ላይ ተጽዕኖ ያሳረፉትን፣ የሚነገር መሳጭ ታሪክ ያላቸውን፣ ወሳኝ የሆነ ስኬት ያሰመዘገቡትን፣ ዜና መሆን ባይችሉም በማኅበረሰባቸው ላይ ተጽዕኖ ያሳረፉትን እንመርጣለን።
የስም ዝርዝሮቹ ከዚህ ዓመት መሪ ቃል፣ ጥንካሬ ጋር መመሳከራቸውን ማሳወቅ እንወዳለን። በዚህ ዓመት የተመረጡት ሴቶች በጥንካሬያቸው ለለውጥ የሚወተውቱ እንዲሁም የማኅበረሰባቸውን ሕይወት ወይንም በዓለም አቀፍ ደረጃ መሻሻሎች እንዲኖሩ የሰሩ ናቸው። በአየር ጠባይ ለውጥ ላይ የሚሰሩ ሴቶችን ለማካተት፣ ከአየር ጠባይ ለውጥ መብት ተሟጋቾች መካከል ፈር ቀዳጅ የሆኑትን እና የአካባቢ ጥበቃ መሪዎችን መርጠናል።
ከሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ወካይ የሆኑ የፖለቲካ ክፍሎችን፣ በተቃራኒው ደግሞ በጋራ የማያስማሙ ስሞችን ድምጽ ወክለናል።
የመጨረሻዎቹ ስሞች ቀጣናዊ ውክልና እንዳላቸው እንዲሁም ከመመረጣቸው በፊት ፈቃዳቸውን ለማግኘት ተሞክሯል። ሁሉም ሴቶች በዝርዝሩ ውስጥ ለመካተት ፈቃደኛ መሆናቸውን አሳውቀዋል።
የቢቢሲ 100 ሴቶች ፕሮዳክሽን አባላት ቫለሪ ፔራሶ፣ ናታሊያ ፒያንዞላ፣ ማሪያ ዛካሮ፣ ሬቤካ ቶርን፣ ላራ ኦዌን፣ ናታሻ ፈርናንዴስ፣ ኒአም ሁጌስ፣ አህመን ካሃዋጃ፣ ሻንያ ኦፕንሀይመር፣ ሳራ ቲያሚዩ እና ሩባብ ባቶል
ተጨማሪ የፕሮዳክሽን ድጋፍ፡ ቫንዳራ ቪጄይ፣ ካቴረይና ኪንኩሎቫ፣ ማሪያም አማን፣ ቬራ ክዋኮፊ፣ ሞውና ባ፣ ሩፓ ሣ፣ ጁሊያን ኤል-ሀጂ፣ ማርክ ሺያ፣ ክሪስ ክሌይቶን፣ ዩና ኩ፣ ኢሳሪያ ፕራይትቶንጊያም፣ ፓውላ አዳሞ ኢዶኤታ፣ ላውራ ጋርሺያ፣ አና ፓይስ፣ ዣና ቤዝፒያቹክ፣ ዝላታ ኦኑፍሪቫ፣ ቤርዛ ሲምሴክ፣ ፋርሃት ጃቬድ፣ አናስታሲያ ሶሮቃ፣ ታይስ ካራንካ፣ ሴሌስቲን ካሮኒ፣ ሻህኔዋዝ ሮኪ፣ ኻይሩላ ኡባይዱላቭ፣ አብዲቤክ ካዚየቭ፣ ካትሪና ቴሴ፣ ሲልቪያ ቻንግ፣ ላውራ ቢከር፣ አይ ቱ ሳን፣ ቡይ ቱ፣ ዶ ሁንግ፣ ፋርዛድ ሴይፊካራን
የቢቢሲ 100 ሴቶች ኤዲተር ጎልኖሽ ጎልሻኒ
ኤክስኪውቲቭ ኤዲተር፡ ክሌር ዊሊያምስ
ኮሚሽኒንግ ኤዲተር፡ ፊዮና ክራክ
ለወርልድ ሰርቪስ ቋንቋዎች ፕሮዳክሽን ራፋኤል ቻኮን፣ ፒፕ ጆይ እና ካሮል ኦላና
ዲዛይን፡ ሊሊ ሁይንህ፣ ፕሪና ሻህ፣ ጄኒ ሎው፣ ማት ቶማስ፣ ፓውሊን ዊልሰን እና ኦሊ ፓውል
ዴቬሎፕመንት፡ ስኮት ጃርቪስ፣ አሩን ብሃሪ፣ አሌክሳንደር ኢቫኖቭ፣ ማቲው ቴይለር እና ፕሪቲ ቫጌላ
የፎቶ ባለመብቶች፡ ጌቲ ኢሜጅስ፣ ሎረን ሃርሊ/ 10 ዳውኒንግ ስትሪት፣ ትሬሲ ኢሚን፣ ዮሺሞቶ ኢንቴርቴይመንት፣ ዩናይትድ ወርልድ ሬስሊንግ፣ ስቴፋኒ ኪንግ፣ ዴሪክ ኢቫንስ፣ አስታ ክሪስትጃንስ፣ ሻህኔዋዝ ሮኪ፣ አኔት ሆርኒሸር፣ ፋርሂዮ መሀመድ ሁሴን፣ ቢልሳትያ፣ ሞሃናድ ኤልሁሴን፣ ማታራ ስቶክስ፣ ጆ ኦ ሻውኒሲ፣ታፓስ ማልሊክ፣ @KuchuTimes፣ ሜላኖማ ኢንስቲትዩት አውስትራሊያ፣ ክሪስቶፈር ሚሼል፣ ሊያ፣ ኤም. ስቬን ቶርፊን፣ ሙንዴሌ ባዲሙቡንጊ አላይን፣ዩኤስኤ አርቸሪ፣ዳርያና ላቭሬንኮ፣ ኮ ኦ፣አሊክስ ማኪንቶሽ፣ስቲቭ ጄራርድ፣ ኬሊስ ፖርቲሎ፣ ባንኮክ ኩራት፣ ማሪያና ካስቲየራስ፣ የዲያስፖራ አርትስ ግንኙነት፣ አሲዮን ኢንተርና፣ሁዋን ፓብሎ ኦርላና፣ ዣን ፍራንሷ ካርሊ ለካትሪን፣ ሃምኔት/ሳምሰንግ ግሎባል ሲሪስ፣ ፔዥ ሴንሳል/የሄይቲ ብሪጅ አሊያንስ፣ጎንዛሎ ማርሮኪን፣ ራጅ ኩማር ሽሬስታ፣ ራቭሻን ሙሴይቭ፣ ኤች ኬ ስቱዲዮ፣ ሊዛ ፓሎሚኖ፣ ሃሮልድ ሌቪን፣ ሚዲያ ዌልስ፣ኔንሲ ራጋብ፣ አሌክሳንደር ኑኒስ፣ ማኖን ኦቤል/ክላንዴስቲና፣ ሂላ ሺሎኒ/የግድግዳ ሴቶች፣ ፊሊክስ ስፔለር/ንድፍ ሙዚየም፣ ካዚም ኪዚል፣ ሁጎ ማቲ፣ዲሚትሪ አይቹቫኮቭ፣ ኡላ ኦስማን፣ ናቨር ስፖርት፣ ናሳ፣ ፒተር ጆዳኖ፣ ዬሮ አዱኛ፣ ጁማዲል ቶኮጆዬቭ፣ ማርኮ ኮንቲ ሲኪች፣ፍራንሷ ባሬሬ፣ ሶሻል ፈንድ ፎር ዴቬሎፕመንት፣ቤን ኮኸን፣ ሃጋር ባደር/ላባ ኢምፓክት ሃውስ፣ ኬይኮ አቱታ፣ ዶአን ዱክ ታንግ፣ እጩዎች